Fana: At a Speed of Life!

ከሃዲው ቡድን በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን ቀጥሎበታል – ምክትል ጠ/ሚ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በምድር ላይ ያሉ የመጨረሻ የክፋት መገለጫዎችን ከመፈፀም ወደ ኋላ የማይመለሰው ይህ የህወሓት ቡድን በተለያዩ ክልሎች ፅንፈኞች እና አሸባሪዎችን እያስተባበረ፣ ስምሪት እየሰጠ እና በፋይናንስ እየደገፈ በማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት መፈፀሙን እንደቀጠለበት የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አስታወቁ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ በማይካድራ አካባቢ በንፁኃን ዜጎች ላይ የደረሰው እጅግ ልብ ሰባሪ፣ ኢ ሰብዓዊ እና ፍፁም አሳዛኝ ዘር ተኮር ጥቃት በከሃዲው ቡድን አስተባባሪነት የተፈፀመ ይቅር የማይባል ወንጀል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ይህ ጭፍጨፋ እጅግ ሰው መሆንን ጥያቄ ውስጥ የሚከት ዘግናኝ ድርጊት ነውም ብለዋል፡፡

ሁሉም እንደታዘበው ከሃዲው ቡድን ከቀናት በፊት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈፀመው አሳዛኝ ጥቃት ሳይበቃው አሁንም በንፁኃን ዜጎች ላይ የዘር ማጥፋት እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ ገፍቶበታልም ነው ያሉት፡፡

እኩይ ድርጊቱን የቀጠለበት ዓብይ ምክንያት የኢትዮጵያውያንን አንድነት እና የአብሮነት ክብር ለማዋረድ ቆርጦ የተነሳበትን ዓላማ እስከመጨሻዋ ሰዓት ድረስ ለማስፈፀም መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘመናት ገፀ-ብዙ ፈተናዎች ያሳለፈች ሃገር ብትሆንም፤ በታሪኳ እንደህወሓት ዓይነት የወጣለት አረመኔ እና የጭካኔ ጫፍ የተቆናጠጠ ወንጀለኛ ቡድን ገጥሟት አያውቅም ለማለት ይቻላል፡፡

ይህ ቡድን ከአፈጣጠሩ ጀምሮ ፀረ-ኢትዮጵያ የሆነ የተግባር ስሪት አራማጅ እንዲሁም ፀረ-አማራ የሆነ የአስተሳሰብ ቅኝት ወላጅ ሆኖ ለበርካታ ዓመታት ሰፊውን ማህበረሰብ ሲያደናግር መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

በተፈጠረበት ቅኝት እና ባደገበት ስሪት ሁልጊዜ “የበላይ” ሆኖ ለመኖር ካለው የተንጠራራ ምኞት፤ ከሌሎች የሃገሪቱ ህዝቦች ጋር በእኩልነት መራመድ ውርደት ስለሚመስለው “ጥፋት”ን የስነ-ልቦና ስብራቱ ማካካሻ አድርጎት ዘልቋልም ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡

በአሁን ሰዓት ሃገሪቱ በእጅጉ ፍትህን ተጠምታለች፤ ህዝብ እና መንግስት በጀመሩት የጋራ ርብርብ የከሃዲያኑን ስብስብ በፍጥነት ወደ ህግ ያቀርቡታል፤ እንዲሁም በማያዳግም ሁኔታ ያስወግዱታልም ብለዋል፡፡

አሁንም ከሃዲ ቡድኑ በአንድ በኩል “ሰላም” በሌላ በኩል “ጥፋት” እያጣቀሰ ጊዜ ለመግዛት የሚያደርገው ጥረት ብዙ ርቀት የሚያደርስ ባለመሆኑ፤ ለዕውነት እና ለፍትህ መረጋገጥ ሲባል መንግስት የጀመረው ህግና ስርዓት የማስከበር ዘመቻ እስከመጨረሻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አውስተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.