Fana: At a Speed of Life!

ከህወሓትና ከኦነግ ሸኔ አመራሮች ተልዕኮ ተቀብለው ሲሰሩ ነበር የተባሉ ተጠርጣሪ ክስ ተመሰረተባቸው

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 18 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ህገ መንግስቱና ህገመንግስታዊ ስርአቱ እንዲፈርስ ከህወሓትና ከኦነግ ሸኔ የፀረሰላም ቡድን አመራሮች ተልዕኮ ተቀብለው ሲሰሩ ነበር የተባሉት አቶ አለም ደስታ ሃየሎም ክስ ተመሰረተባቸው

አቶ አለም ደስታ ሃየሎም ክስ የተመሰረተባቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲሆን ÷ተከሳሹ ችሎት ተገኝተው የመኖሪያ አድራሻቸውን እና እድሜያቸውን አስመዝግበዋል።

በጋምቤላ ክልል በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩት ባለሃብት አቶ አለም ደስታ ሃየሎም አንደኛ ደረጃም ሆነ ምንም አይነት ትምህርት እንዳልተማሩ ለችሎቱ ገልጸዋል።

ክሱ በችሎት እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲሆን ተከሳሹ ጠበቃቸው በተገኙበት ክሱ እንዲታይላቸው ጠይቀዋል።

በተከሳሹ ላይ ዐቃቤ ህግ የመሰረተው ክስ እንደሚያመላክተው ተከሳሹ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀፅ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም 238 (1) ለ እና (2)ን በመተላለፍ  ከግብረ አበሮቻቸው ጋር በዋና ወንጀል ተካፋይ በመሆን ህገ መንግስትና ህገመንግስታዊ ስርአቱ እንዲፈርስ ከህወሓትና ከኦነግ ሸኔ የፀረሰላም ቡድን አመራሮች ተልዕኮ ተቀብለው  ሲንቀሳቀሱ ነበር ብሏል ።

በዚህም ከጥር 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ክልል እንዳይረጋጋ እና ክልሉ የጦርነት ማዕከል  እንዲሆን እንዲሁም የፌደራል መንግስት እንዲፈርስና የመንግስት ስልጣንን ከህገ መንግስት ስርአት ውጪ በሆነ መንገድ ለመያዝ በማሰብ ሲሰሩ እንደነበር በክሱ ተመላክቷል።

በተጨማሪም ተከሳሹ በምዕራብ ወለጋ የሚገኘውን የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችን ጎብኝተው ወደ ጋምቤላ መመለሳቸውን በክሱ የጠቀሰው ዐቃቤ ህግ ÷ ታጣቂዎቹ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ጦርነት ላይ ናቸው ስለዚህ አስቸኳይ ድጋፍ እየፈለጉ ስለሚገኙ በህወሓት በኩል የሚደረግላቸው ድጋፍ በአጭር ጊዜ ይሁን ማለታቸውም ተመላክቷል።

በሰኔ 16 ቀን 2012 ዓ.ም የኦነግ ሸኔ ተወካይ ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩና እና ወደ አዲስ አባባ ከተማ እንደሚልኩም በስልክ ለዶክተር ደብረፂዮን ገብረሚካኤል የገለጹ መሆናቸውም በክሱ ተጠቅሷል።

በሌላ በኩል ደግሞ ተከሳሹ ሰኔ 19 ቀን 2012 ዓ.ም በህወሓት በኩል ለኦነግ ሸኔ ቡድን ስለሚደረገው የገንዘብና የቁሳቁስ  ድጋፍ ለመነጋገር ለኦነግ ሸኔ ቡድን ተወካይ አዲስ አበባ ድረስ መምጣታቸው  የህወሓት ከፍተኛ አመራር ከሆኑት ከዶክተር አዲስ አለም ባሌማ ጋር በሚሰሩበት መንገድ  ትራንስፖርት ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት የኢትዮጵያ ፖስታ ኢንስቲቲዩት አምስተኛ ፎቅ መግባታቸውንም  ዐቃቤ ህግ አስረድቷል።

የኦነግ ሸኔ ቡድን ከህወሓት ባገኘው የተለያዩ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ ድጋፍ ኦሮሚያ ክልል ምርጫ አይካሄድም፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሃል ሃገር  ገብተን ስልጣን በሃይል እንይዛለን ብለው መግለጫ በመስጠት  ማሳወቃቸውም ተጠቅሷል።

በ2012 እና በ2013 ዓ.ም በተለያዩ ወራቶችና ቀናቶች በምእራብ ወለጋ፣ ኢሉባቦር ዞኖች ፣ በሃገር መከላከያ ሰራዊትና በክልሉ የጸጥታ ሃይሎች እንዲሁም በንፁሃን ላይ ጦርነት በመክፈት ከፍተኛ የፀጥታና ሰብአዊ ቀውስ በአካባቢው ንፁሃን ዜጎች ላይ እንዲደርስ ማድረጋቸውም ተመላክቷል።

በተለያዩ የወረዳና የቀበሌ መዋቅር እንዲፈርስ በተለይም በጥቅምት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በምእራብ ወለጋ ዞን ጉሊሶ ወረዳ ጋዎ ጋነቃ ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ 36 የሚሆኑ ንጹሃን ዜጎች እንዲገደሉ እና 229 አባወራዎች ከቀያቸውና ከንብረታቸው ተፈናቀለው ለከፍተኛ ቀውስ እንዲዳረጉ ያደረጉ መሆኑም ነው የተጠቀሰው ።

ሚያዚያ 8 ቀን 2012 ዓ.ም ከህዳሴ ግድብ ድርድር ጋር ተያይዞ የግብፅ መንግስት ድርድሩን አልቀበልም ብሎ አውሮፕላን ወደ  ደቡብ ሱዳን እያስገባ በመሆኑ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ቀለበት ውስጥ ነው ብለው በመግለጽ  በወቅቱ ትግራይ ክልል ከባድ የጦር መሳሪያ የሚጭኑ 40 ፒካፕ መኪና እና የርቀት መገናኛ ሬዲዮ ቱር ጭምር ገዝተው ለጦርነት ማዘጋጀት እንዳለባቸው ለሕወሓት ከፍተኛ አመራር ለሆኑት ለአቶ ስብሃት ነጋ መግለጻቸው እና ስብሃትም መስማማታቸውን ዐቃቤ ህግ በዝርዝር ክሱ አመላክቷል።

በዶክተር ደብረ ፂዮን ገብረሚካኤል የሚመራ የትግራይ ክልል አስተዳደር ምክርቤት ካቢኔ ጦርነት አውጆ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ሰራዊት ላይ ጥቃትና እና የንብረት ዝርፊያ በመፈጸም ከፍተኛ ቀውስ መፍጠራቸው በክሱ ተጠቅሷል።

በዚህ መልኩ ህገመንግስቱ ላይ በመፈጸም ወንጀል የተከሰሱት ግለሰብ ከጠበቃቸው ጋር እንዲታይላቸው በጠየቁት መሰረት ፍርድ ቤቱም በይደር ለነገ ለመመልከት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በታሪክ አዱኛወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.