Fana: At a Speed of Life!

ከነገ ጀምሮ ከ100 ሺህ ብር በላይ አዲሱን የገንዘብ ኖት በአሮጌው ገንዘብ ኖት መቀየር አይቻልም

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ከነገው ዕለት ጀምሮ ከ100 ሺህ ብር በላይ አዲሱን የገንዘብ ኖት በአሮጌው ገንዘብ ኖት መቀየር እንደማይቻል ተገለፀ፡፡

መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም የጀመረውን የገንዘብ ቅያሬ ሂደትን አስመልክቶ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ እና የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይም ባለፈው አንድ ወር የነበረው የገንዘብ ቅያሬ ሂደት ውጤታማ እንደነበረ ነው የተናገሩት።

የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ወደ ሚገኙ የመንግስት እና የግል ባንክ ቅርንጫፎች 96 ቢሊየን ብር አዲሱ የገንዘብ ኖት መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

 

በዚህም ከ920 ሺህ በላይ አዳዲስ የባንክ አካውንቶች እንደተከፈቱ የገለፁት ገዢው ከባንክ ውጭ ሲዘዋወር የነበረ 31 ቢሊየን ብር ወደ ባንክ ሊገባ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም የባንክ አካውንት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ከማሳደጉ ባሻገር ያለአግባብ ሲዘዋወር የነበረውን ህገ ጥ ገንዘብ ወደ ህጋዊ ስርዓት እንደመለሰውም አንስተዋል።

ዶክተር ይናገር ከ100 ሺህ እስከ 1 ነጥብ 5 ሚለየን ብር ያለው የገንዘብ ቅያሬ የጊዜ ገደብ ዛሬ ማብቃቱን ተከትሎ ከዚህ በኋላ የመቀየር ሂደቱ ከ100 ሺህ ብር በታች መሆኑን ገልፀዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የአንድ ወር የገንዘብ ለውጥ ሂደቱ ስኬታማ እንደነበረ ያነሱ ሲሆን ከህጋዊ መንገድ ውጭ ሲዘዋወር የነበረ በርካታ ገንዝብ ወደ ህጋዊ ስርዓቱ መግባቱን ተከትሎ የሀገሪቱ መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ጤናማ በሆነ መልኩ እየሄደ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ለዚህም ከህዝቡ በተጨማሪ የንግዱ ማህበረሰብ አሮጌውን ገንዘብ በአዲሱ የገንዘብ ኖት ለመቀየር በየቀኑ በማስገባት ትልቅ አስተዋፅኦ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት።

ከዚህ በኋላም መረጃ ላልደረሳቸውን የአርብቶ አደር እና አርሶ አደር የህብረተሰብ ክፍል አዲሱ የገንዘብ ኖት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራም አውስተዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ እንዳሉት የብር ኖቱን ወደ ተገቢው ቦታ ለማጓጓዝ እና ህገ ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር የመከላከያ ሠራዊቱን ጨምሮ ሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ውጤታማ ተልዕኮ ፈፅመዋል፡፡

በቀጣይም የብር ደህንነትን ለመጠበቅ እና ቅይይሩ የተሳካ እንዲሆን ከመከላከያ ሠራዊት እና ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ብዙ ይጠበቃልም ነው ያሉት፡፡

ሆኖም በሂደቱ ሁለት መጠነኛ ችግሮች መስተዋላቸውን ያነሱት ሚኒስትሩ ከሀሰተኛ የገንዘብ ኖት (ፎርጂድ) ጋር በተያያዘዘ በአማራ ክልል፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአዲስ አበባ እና በደቡብ አንዳንድ ምልክቶች ተስተውለው የነበሩ ሲሆን የፀጥታ ግብረ ሀይሉ በጥምረት ባከናወነው ስራ ድርጊቱን መቆጣጠር መቻሉን አስረድተዋል።

በተለይም በአማራ ክልል ማሽን ተክለው ሀሰተኛ የብር ኖት ሲያትሙ የነበሩ አካላት ከእነማሽናቸው በመያዙ በኩል የአማራ ክልል የፀጥታ ሀይል ከሌሎች የፀጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ለሰራው ስራ ምስጋና አቅርበዋል።

በፀጋዬ ንጉስ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.