Fana: At a Speed of Life!

ከአንድ ላም በአማካይ የሚገኘውን ወተት ወደ 30 ሊትር ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሀብት ልማት ፕሮጀክት መጀመር የሚያስችል የሶስትዮሽ ስምምነት ተፈረመ።

ስምምነቱን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ፣ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህና የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አስራት አፀደወይን ተፈራርመውታል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሃብት ልማት ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የወተትና የስጋ ምርትና አቅርቦት በማሳደግ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ተስፋ የተጣለበት ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ላሞች አማካይ የወተት ምርት በአንድ ላም በቀን 1 ነጥብ 8 ሊትር ሲሆን፥ በፕሮጀክቱ ወደ 30 ሊትር የማሳደግ እቅድ ተይዟል።

ፕሮጀክቱ የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል፣ ለስጋና ለወተት ምርት የሚሆን መኖ አዘገጃጀት፣ የእንስሳት ጤና አጠባበቅ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት አረባብ እና የገበያ ትስስርን የሚያካትት ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የኢትዮጵያ ዋና የኢኮኖሚ ምንጭ የሆነውን ግብርና የእንስሳት ሀብትን በቴክኖሎጂ ለማዘመን ከክልል መንግስታት፣ በየክልሉ ከሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እና በየአካባቢው ከሚገኙ አርሶ አደሮች ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ብትሆንም ምርቱ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪና ጥራቱን የጠበቀ ባለመሆኑ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነች ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ የእንስሳት ሃብት ልማት ፕሮጀክት በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በጋምቤላና በሶማሌ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.