Fana: At a Speed of Life!

ከስምምነቱ በተጻራሪ የምድር ሙቀት ጨምሯል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ6 ዓመት በፊት 196 ሀገራት የምድርን ሙቀት በ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመቀነስ፣ በፈረንሳይ በተደረሰው “የአየር ንብረት ስምምነት” ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል፡፡

ይሁንና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአካባቢ ፕሮግራም ይፋ እንዳደረገው ÷ ሀገራቱ የስምምነት ፊርማቸውን ባላከበረ መልኩ የድንጋይ ከሰል ምርታቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መጥተዋል፡፡

ድርጅቱ በሪፖርቱ እንዳመላከተው ÷ ሀገራቱ ለቀጣይ 10 ዓመታት ሊያመርቱ ከተስማሙትና ፊርማቸውን ካኖሩበት ሰነድ ውስጥ ከተመለከተው የድንጋይ ከሰል ምርት መጠን በ240 በመቶ አብላጫ ያለው ምርት አምርተዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገራቱ በስምምነት ሰነዱ ከተስማሙበት የነዳጅ ዘይት ምርት መጠን በ57 በመቶ አብላጫ ያለው ምርት እንዲሁም በ71 በመቶ አብላጫ ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ማምረታቸው ነው በሪፖርት የቀረበው፡፡

እንደ ተመድ ÷ ምንም እንኳን በስምምነቱ የምድርን ሙቀት በ 1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ለመቀነስ ሀገራቱ ፊርማቸውን ቢያኖሩም በተጻራሪው ምድራችን በ 1 ነጥብ 1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ያለ ሙቀት አስመዝግባለች፤ ሀገራቱም የነዳጅ ዘይት፣ የድንጋይ ከሰል እና የተፈጥሮ ጋዝ ምርታቸውን ከመቀነስ ይልቅ በአደገኛ ሁኔታ ከእጥፍ በላይ ለማምረት ተዘጋጅተዋል ብሏል፡፡

ሀገራቱ እስከ ፈረንጆቹ 2040 የሚያመርቱትን የድንጋይ ከሰል ምርት እንደሚያሳድጉም አመላካች መረጃዎች እንዳሉ መጠቁሙን ሲጂቲ ኤን ዘግቧል፡፡

በዓለማየሁ ገረመው

 

 

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.