Fana: At a Speed of Life!

ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት በኢትዮጵያ ፌዴራዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ህገ መንግስት አንቀጽ 87 በተደነገጉ ግልጽ መርሆዎች መከላከያ ሰራዊት አዋጅ ቁጥር 1100/2011 በተሰጡት ግዳጆች መሰረት ዝርዝር ተልዕኮዎችን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንቦች እና መመሪያዎችን በማውጣት በሃገራችን ላይ የተቃጡ የውጭና የውስጥ ጥቃቶችን በመመከት የሃገራችንን ሉዓላዊነት አስከብሯል። የህዝብንም ሰላም በማስጠበቅ ላይ ይገኛል።

መከላከያ ሰራዊቱ የአፍሪካውያን ወንድሞቻችን ሰላም የእኛም ሰላም ነው በሚል መርህ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት በሰላም ማስከበር ተልዕኮ ላይ ተሰማርቶ ዛሬም ግዳጁን በአስደናቂ ሁኔታ በመወጣት ላይ ይገኛል። ከሁሉም በላይ የዓለም ህዝቦችና የቀጠናችን ብሎም የሃገራችን ዋነኛ ጠላት የሆነውን አሸባሪነት ለመዋጋት በጎረቤት ሃገር ሶማሊያ የመሸገውን የአልሸባብ አሸባሪ ቡድን በመመከት ቀጠናችን ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ እንዲሆን መስዋዕትነት በመክፈል ላይ ነው።

በሃገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሚነሱ አለመረጋጋቶችን ከሌሎች የሃገራችን የፀጥታ ሃይሎች፣ ከክልል መስተዳድሮች፣ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከሃገር ሽማግሌዎችና በዋነኝነት ከህዝባችን ጋር በመተባባር ችግሩን ለመቅረፍ ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲመጣ ሰርቷል፤ አሁንም በመስራት ላይ ይገኛል። በዚህ ተግባሩ ሰራዊታችን በደረሰበት ቦታ ሁሉ ህዝብ ከፍተኛ የሰላም አየር የሚተነፍስ እና እፎይታ የሚሰማው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝቦች ህያው ምስክር ናቸው።

ከእነዚህ የሰራዊቱ አኩሪ ድሎች የምንረዳው ነገር ቢኖር ሰራዊታችን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በአንድ ጊዜ ግዳጆችን መወጣት የሚችል፣ ለፈተናዎች የማይበገር፣ ለሃገር ሉዓላዊነት እና ለህዝቦች ሰላም ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት ከመክፈል ወደ ኋላ የማይል ህዝባችን የሚመካበት ሰራዊት መሆኑን ነው።

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች

የመከላከያ ሰራዊታችን የተጋድሎና የአሸናፊነት ገድሉ በወታደራዊ ስምሪት እና የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ብቻ ሳይገደብ የህዝብ ችግር ችግሬ ነው የሚል የህዝቦች ደህንነትና ኋላ ቀርነት የሚያንገበግበውና የሚቆጨው ያለውን ሁሉ ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል፣ የህዝባችን አለኝታ የሆነ የልማትና የሰላም ሰራዊት ነው። የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የአንድነትና የጥንካሬ መለያ የሆነውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ገንብቶ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ጥረት ሰራዊቱ ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለግድቡ ግንባታ ከወር ደመወዙ በማዋጣት በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ አስተዋጽኦ ከማበርከት አልፎ በግድቡ ላይ ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም አይነት ጥቃት ለመመከት ሌት ተቀን ዘብ ቆሞ በመጠበቅ ላይ ይገኛል። መከላከያ ሰራዊታችን ከራሱ በፊት ለህዝቡና ለሃገር የሚለውን እሴት መሰረት በማድረግ የሃገራችን ህዝቦች ለገጠማቸው ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን አብነት የሚሆን ተግባር እየፈጸመ ይገኛል።

በጎርፍ አደጋ ዜጎች የሚደርስባቸውን አደጋ ለመቀነስ፣ በደም ልገሳ መርሃ ግብር ላይ በመሳተፍ፣ በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሰማርቶ በማገዝ፣ በተፈጥሮ ጥበቃ ላይ ጉልህ ተሳትፎ በማድረግ፣ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ የሆነውን ኮቪድ19 በሽታን ለመከላከል፣ ከደመወዙ ቀንሶ ለአቅመ ደካሞች ድጋፍ በማድረግ፣ ገበታ ለሃገር ፕሮጀከት እውን እንዲሆን የወር ደመወዙን በማዋጣት እና በሃገራችን በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰተውን የአንበጣ ወረርሽኝ ከህዝቡ ጋር በመሆን በመከላከል ከፍተኛ ጥረት ያደረገና በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህ ህዝባዊነቱን ያስመሰከረ ተግባሩን ከመጀመሪያውኑ ሰራዊቱ የታነጸበት መሰረታዊ ባህሪው መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ሃቅ ነው።

መከላከያ ሰራዊታችን ሃገራዊ ግዳጆቹን ሲወጣና ህዝባዊ ተግባራቱን ሲያከናውን የሚገጥሙትን ችግሮች ሁሉ በመቋቋም ፈተናዎችን በጽናት ተጋፍጦ በማለፍና ውድ ህይወቱን መስዋዕት በማድረግም ጭምር መሆኑ በህዝባችን የሚታወቅ ሃቅ ነው። ይሁን እንጅ ሰራዊቱ የሃገሪቱን ሉዓላዊነትና የህዝቦችን ሰላም የማረጋገጥ ህገ መንግስታዊ ተልዕኮውን በጀግንነትና በቁርጠኝነት እየተወጣ ባለበት በዚህ ሰአት የሃገራችንን ሰላምና ደህንነት የማይፈልጉ ቡድናዊና ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የሰራዊቱን ስምና ዝና በማጠልሸት በመርህና በህግ ላይ ያልተመሰረተ የትችት ናዳ በማውረድ ላይ የሚገኙ ቢሆንም ሰራዊቱ ይህን የፀረ ሰላም ሃይሎች አጀንዳ በውል በመገንዘብ ትኩረቱን ግዳጁ ላይ ብቻ በማድረግ እየሰራ ይገኛል።

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ህዝቦች

ሰሞኑን በተለያዩ የትግራይ መገናኛ ብዙሃን ወቅታዊ የአቋም መግለጫ በሚል ርዕስ ስር መግለጫ ያወጣው አካል ሰራዊቱን የሚመለከቱ ጉዳዮች የተካተቱበት ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ አሰራጭቷል። በዚህ መግለጫ 1ኛ ተራ ቁጥር ላይ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 87(5) ድንጋጌ መሰረት የመከላከያ ሰራዊቱ ተግባር ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ በሆነ አኳኋን እንደሚያከናውን የተደነገገውን መርህ በሚጥስ መልኩ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሃይሎች ተወያይተው ከሚሰጡት መፍትሄ ውጭ መከላከያ የአደረጃጃት፣ የስምሪትና የቁጥጥር ተግባሩን መፈጸም አይችልም በማለት መከላከያ በተቋማዊ እቅዱ እንዲሁም ወቅታዊና ሃገራዊ የደህንነት ስጋቶችን መነሻ አድርጎ ግዳጁን እንዳይፈጽም በሚገድብ አኳኋን የተዛባ ይዘት ያለው መግለጫ አውጥቷል።

በዚህ መግለጫ ተራ ቁጥር 5 ላይ ደግሞ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የሃገር ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነት አደጋ ላይ የወደቀ በዝምታ እንዳለፈና የህገ ወጥ የፖለቲካ ሃይሎች ጥቅም አስጠባቂ ሃይል መሆኑን የሚገልጽ መልዕክት በመግለጫ ላይ ተካቷል። እውነታው የመከላከያ ሰራዊታችን የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ተሰማርቶ አስፈላጊ ተገቢና ህጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኝ ቢሆንም ይህንን በተጻረረ መልኩ ሰራዊቱ ህዝብን እየጨፈጨፈ ነው በማለት የመከላከያ ሃይሉን የማይመጥን፤ ተቋሙ ለሃገርና ለህዝብ የከፈለውን እና እየከፈለ ያለውን ክብር መስዋዕትነት የሚያንኳስስ ሃገራዊ ተልዕኮውን እና አኩሪ ታሪኩን የሚያጠልሽ መልዕክት ይህ አካል ባወጣው መግለጫ ተስተጋብቷል። ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ አንዳንድ ግለሰቦች እና ባለስልጣናት በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ይህ አካል መከላከያን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ በማስተጋባት ፍጹም የሰራዊቱን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮ በማራከስ ተግባር ላይ ተጠምደው ይገኛሉ።

ይህ ተግባር መከላከያ ሰሰራዊቱ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች እና በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል ከክልሉ ህዝብ ጋር ከፍተኛ ጥረት በሚያደርግበት የክልሉ ህዝብ የኮቪድ19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ትርጉም ባለው ደረጃ ህዝባዊ ወገንተኝነቱን እያስመሰከረ ባለበት እና አጠቃላይ በክልሉ ያለውን ስምሪት የሃገርን ሉዓላዊነት ለማስከበር አላማ አድርጎ ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁነቱን ባረጋገጠበት ወቅት የሰራዊቱን ተልዕኮ የሚገድብ መግለጫ ማውጣቱ አግባብነት የጎደለው ተግባር ሆኖ አግኝተነዋል።

ይህ መግለጫ የሰራዊቱን ተልዕኮ ያላገናዘበ፣ ግዳጁንም ተንቀሳቅሶ እንዳይፈጽም የሚያስተጓጉል ሃገራዊና ክልላዊ ተግባሮቹንም በአግባቡ እንዳይወጣ የሚያደናቅፍ ሃላፊነት የጎደለው መግለጫ ነው።

ከዚህ በፊትም እነዚህ አካላት ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች በማስተላለፍ ላይ የነበሩ ቢሆንም ለህዝቦች ክብር እና ጥቅም ሲባል በከፍተኛ ሃላፊነት መንፈስ ለማለፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። መላው የሃገራችን ህዝቦች እንደሚገነዘቡት የመከላከያ ሰራዊታችን የማንም ፖለቲካ ሃይል¸ክልል ወይንም ቡድን ጉዳይ አስፈጻሚ ሳይሆን የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሉዓላዊነታቸውን እንዲያስከብርላቸው¸ሰላምና ደህንነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው የገነቡት ጠንካራ፣ ብሄራዊና ሃገራዊ ተቋም ነው። ስለሆነም የሰራዊቱን አደረጃጀት¸ስምሪትና የግዳጅ አፈጻጸም የሚመለከቱ ጉዳዮችን ሰራዊቱ በህገ መንግስቱ የተቀመጠለትን መርህና በአዋጅ የተሰጠውና ግዳጅና ተልዕኮ መሰረት በማድረግ ተግባራቱን በራሱ የሚወስን እንጅ የሰራዊቱን አጠቃላይ ተልዕኮ እኔ ነኝ የምወስንልህ በሚል አግባብ ይህ አካል የሰጠው መግለጫ የሰራዊቱን ገለልተኝነት የሚጋፋ ግልጽ የሆነ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት መግለጫ ሆኖ አግኝተነዋል።

ይህ ወቅት የሃገራችን ህዝቦች እንደ ሃገር የገጠማቸውን ሰው ሰራሽ እና ተፈጥሯዊ ችግሮች በመመከት ሰላማቸውን ለማረጋገጥና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ደፋ ቀና በሚሉበት ወቅት የሃገራችንን እድገት የማይፈልጉ አካላት በተለይ ከህዳሴ ግድባችን ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በግልጽ በሚጻረር መልኩ በእጅ አዙር እና በቀጥታ ጥቃት የሚፈጽሙበትና አንዳንድ ፀረ ሰላም ሃይሎች ሃገራችንን ወደለየለት ትርምስ ለማስገባት አላማ አድርገው በሃገራችን የተለያዩ ክፍሎች በዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ እና የማፈናቀል ወንጀል በመፈጸም ላይ የሚገኙ መሆኑ ይታወቃል።

መከላከያ ሰራዊት ከህዳሴ ግድብ ጋር የተያያዙ የደህንነት ስጋቶችን ለመመከት የሚያስችል ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ባለበት እና በሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰቱ ግድያዎች እና መፈናቀሎችን ለማስቆም አስቸጋሪ የአየር ፀባይ እና መልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ዘልቆ ሰፊ ስምሪት በማድረግ፤ ክቡር መስዋዕትነትን በመክፈል የህዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ ጥረት በሚያደርግበት በዚህ ወቅት መግለጫውን ያወጣው አካል የሰራዊቱን ወርቃማ እድል በሚያጎድፍ መልኩ ሰራዊቱን በሚመለከት ያሰራጨው መልዕክት ፍጹም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።

ጉዳዩ ከህገ መንግስቱ ጋር በቀጥታ የሚቃረን¸የሃገር መከላከያ ሰራዊት ስምሪት እና ተልዕኮ በምንም መልኩ በአንድ አካል ወይም ቡድን ስር የማይወድቅ ህጋዊና ህገ መንግስታዊ በሆነ አግባብ ብቻ የሚመራ መሆኑን እያስታወቅን መግለጫውን ያወጣው አካል ስህተቱን በይፋ እንዲያርም አጥብቀን እንጠይቃለን። ማንኛውም አካል የሰራዊቱን ተልዕኮ በሚያደናቅፍ አግባብ መግለጫ ከመስጠት እና አላስፈላጊ መልዕክት ከማስተላለፍ እንዲቆጠብም እናሳስባለን።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሃገርና ህዝብ የሰጠንን ህገ መንግስታዊ ተልዕኮ በገባነው ቃልኪዳን መሰረት ከማንኛውም የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነጻ በመሆን፣ ክቡር የሆነውን ህይወታችንን በመክፈል ጭምር የሃገራችንን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን ሰላም ለማስጠበቅ ከመቸውም ጊዜ በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ የምንገኝ መሆኑን ለመላው ህዝባችን እያረጋግጥን የኢትዮጵያ ህዝብ አሁንም እንደወትሮው ሁሉ ከጎናችን ሆኖ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን እንዲቀጥል ጥሪያችንን እናቀርባለን።

መላው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት

እኛ የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት በተጋድሎና በድል የደመቀ አንፀባራቂ ታሪክ ያለን ሰራዊት ነን። በከፍተኛ ህዝባዊ ወገንተኝነትና ፅናት ምድራዊ ፈተና ተቋቁመን እና ጥሰን በማለፍም ለሃገራችን እና ለህዝባችን ሰላም፣ ደህንነትና ልማት ስንል ሁሉንም አይነት መስዋዕትነት እየከፈልን አልፈናል። በቀጣይም ከዚህ ጉዟችን ሊያደናቅፉን የሚጥሩ፣ ከተልዕኳችን ሊገድቡን ከሚሞክሩና አንድነታችንን ሊሸረሽሩ በሚታክቱ ማንኛውም አይነት ሃይሎች ሴራ ሳንገታ ደማቅ ታሪክ መስራታችንን እንቀጥላለን።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.