Fana: At a Speed of Life!

ከወለድ ነጻ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ከ117 ቢሊየን ብር በላይ ቆጥበዋል ተባለ

አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 5 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፋይናንስ አካታችነትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ዕድገት እንዲፋጠን በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ዕውቀት፣ ክህሎትና ሀብታቸውን አስተባብረው እንዲሰሩ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ጥሪ አቀረቡ።

ጥሪው የቀረበው ‘አካታች የፋይናንስ አገልግሎትን በኢትዮጵያ ተደራሽ ማድረግ’ በሚል ርዕስ በተዘጋጀ የከኢድ እስከ ኢድ ማጠቃለያ መርሀ ግብር ላይ ነው።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ባስተላለፉት መልዕክት የፋይናንስ አካታችነትን ለማረጋገጥ መንግስት መሰረታዊ ማሻሻያዎችን ማድረጉን አስታውሰዋል።

ከማሻሻያዎቹ ጋር በተያያዘም የሸሪያ መርህን መሰረት ያደረጉ በርካታ የፋይናንስ ተቋማት ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

ማሻሻያውን ተከትሎ በዘርፉ በተከናወኑ ስራዎች የተገኙ ውጤቶች አበረታች መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት ሁለተኛውን የህግ ማሻሻያ በቅርቡ ማከናወኑን አንስተዋል።

አዲሱ ማሻሻያም ከዚህ በፊት ያልተዳሰሱና ከሸሪያ መርህ ጋር የተጣጣሙ አሰራሮችን እንዳካተተ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን ደስታ በበኩላቸው ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሁለት ትሪሊየን ዶላር በላይ የሚያንቀሳቅስ ዘርፍ መሆኑን ጠቅሰው፥ በዘርፉን በስፋት በመጠቀም እንግሊዝና ጎረቤት ሀገር ኬንያ ተጠቃሽ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከወለድ ነጻ አገልግሎትን ከአስር ዓመት በፊት በመስኮት አገልግሎት ደረጃ መጀመሯን አንስተው፥ ከለውጡ ወዲህ ግን ራሳቸውን ችለው ከወለድ ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ባንኮች ወደ ገበያው እንዲገቡ በመፈደቁ አራት ባንኮች ዘርፉን መቀላቀላቸውን አመላክተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ከ117 ቢሊየን ብር በላይ ቆጥበዋል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ ከወለድ ነጻ የፋይናንስ ስርዓት ምንነትና ጠቀሜታዎቹ ላይ ያተኩሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በዘርፉ ባለሙያዎች ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት መረጃ ያመላክታል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.