Fana: At a Speed of Life!

ከውጭ ኢንቨስመንት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሃምሌ 28፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ)ኢትዮጵያ ከውጭ ኢንቨስትመንት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ማግኘቷን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በቅርቡ ከተሰጠው የቴሌኮም ፈቃድ የተገኘውን የ800 ሚሊየን ዶላር ጨምሮ ነው 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ዶላር ከውጭ ኢንቨስትመንት ያገኘችው፡፡
የተገኘው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ገልፀው፤ በ2012 ዓ.ም. ከውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት በትግራይ ክልል በነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ምክንያት፣ በክልሉ ሁሉም ኢንዱስትሪ ፓርኮች ሥራ ማቆማቸው፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ሲያስተላልፉት የነበረው የሀሰት የመረጃ ሥርጭት ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው ኮሚሽነሯ ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆነንም የተገኘነው ገቢ ትልቅ ስኬት ነው ብለዋል፡፡
የኢንቨስትመንት ኮሚሽነሯ ይህን ያሉት በቅርቡ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ የገቡ ኢንዱስትሪ ፓርኮችንና ሌሎች አማራጮችን አስመልክተው፣ በሥራ ላይ ካሉ የውጭ ባለሀብቶችና መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ ዲፕሎማቶች ጋር ባደረጉት ውይይት ነው፡፡
ኮሚሽነሯ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጡ፣ እንዲሁም የባለሀብቶችን ፍላጎት ያሟሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገንብታለች ሲሉ ለተሰብሳቢዎች ማስረዳታቸውን ከንግድ እና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.