Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከወዲሁ ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የባህርዳር፣ ጅማ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች አስታወቁ።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የባህርዳር፣ ጅማ እና ሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የስራ ሃላፊዎች ተማሪዎቻቸው ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ተምህርታቸውን የሚያደናቅፉ ነገሮች እንዳይኖሩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሰይ ከበደ እንዳሉት÷ ተማሪዎችን በዙር ለመቀበል የሚደረገው ዝግጅት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ማድርግ የሚለው ቀዳሚ ቦታ የተሰጠው ነው፡፡
ከፀጥታ አካላት ጀምሮ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው እና የግቢው ማህበረሰብ፣ የክልል እና ከተማ አስተዳደሩ አመራሮችን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰላምን ለማስፈን ዩኒቨርሲቲው እየሰራ መሆኑም ታውቋል፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ በበኩላቸው ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው ሲመለሱ ስለ ነገ ማሰብ ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
አያይዘውም በዙሪያቸው የሚገኙ አካላት ሰላምን በማስፈን ስራ ላይ ሀላፊነታቸውን መወጣት ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ሰላምን ዘላቂ ማድረግ ደግሞ የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
የሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ ደግሞ የተማሪዎቹን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሮች ቢኖሩ እንኳን በሰላማዊ መንገድ መፍታትን ልምድ ማድረግ ከተማሪው ይጠበቃል የሚሉት ፕሬዚዳንቱ ተማሪዎች ወላጅ የሰጣቸውን አደራ ለመወጣት በሰላም ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደመጡበት እንዲመለሱ በትኩረት እየተሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይም ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪ መስለው የሚገቡ ሰላም አደፍራሽ አካላት አንዳይኖሩ፣ ከተማሪ እና ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ሰራተኞች ውጭ የሚገቡ ካሉም መቆጣር የሚያስችል እና ሰላምን የሚያደፈርሱ አካሄዶችን መቆጣጠር የሚያስችሉ አሰራሮችን እየዘረጉ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በዙፋን ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.