Fana: At a Speed of Life!

ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት በሚያስከትለው የጎርፍ አደጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይባባስ የቅድመ መከላከል ስራቸው በፍጥነት እንዲጠናቀቁ አቶ ደመቀ አሳሰቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሃገሪቱ ከፍተኛ የዝናብ ስርጭት በሚያስከትለው የጎርፍ አደጋ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንዳይባባስ ተጋላጭ የሆኑ ተፋሰሶች የቅድመ መከላከል ስራቸው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

የተፋሰሶች ከፍተኛ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ስብሰባ በምስል ተደግፎ ተካሄዷል።

የምክር ቤቱ ሰብሳቢ የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ እንደተናገሩት፥ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎችን በመለየት እና የቅድመ መከላከል ስራዎችን በፍጥነት ማከናወን ይገባል።

በጎርፍ ምክንያት የሚከሰተው አደጋ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት የተጀመረውን ሃገራዊ ጥረት በእጅጉ እንደሚፈታተነው አስረድተዋል።

ከፊት ለፊት የሚገጥሙ ውስብስብ ችግሮችን አስቀድሞ በቅድመ መከላከል ስራዎች በሚገባ መመከት የሚቻልበትን አቅም ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የማህበረሰቡን ግንዛቤ ጎን ለጎን ማጎልበት ይገባልም ነው ያሉት።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው፥ የቅድመ መከላከል ስራዎች መካከል የወንዝ አቅጣጫ አመራር እና የጎርፍ መከላከል ዳይክ ስራና ጥገና እየተከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የተጠናከረ የግድብ አስተዳደር እና የመረጃ መሰብሰቢያ መሳሪያዎችን ደረጃ የማሳደግ ስራዎች በመከናወን ላይ እንደሆኑም ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ከክልሎች ጋር በመቀናጀት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን አሳሳቢነት ከግንዛቤ በማስገባት፤ ከፍተኛ የጎርፍ ስጋት የተደቀነባቸውን አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት ወጪ ቆጣቢ በሆነ አግባብ የቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲጠናቀቁ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.