Fana: At a Speed of Life!

ከ1 ቢሊየን በላይ የአንድሮይድ ስማርት ስልኮች የመጠለፍ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተባለ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ1 ቢሊየን በላይ የሚሆኑ የአንድሮይድ ስልኮች በደህንነት ማዘመኛ ስለማይጠበቁ የመጠለፍ አደጋ እንደተቀደነባቸው ተገለፀ።

በአንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ላይ የተታየው ክፍተት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በቢሊየን የሚቆጠሩ ስማርት ስልኮች ተጠቃሚዎች ለመረጃ ስርቆት እና ለቫይረስ ጥቃት እንዲጋለጡ ያደርጋቸዋል ነው የተባለው።

በአውሮፓውያኑ 2012 እና ከዚያ በፊት የተመረቱ የአንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ስሪትን የሚጠቀሙ ስማርት ስልክ ያላቸው ሰዎች ጉዳዩን በትኩረት ሊከታተሉት እና ሊጠነቀቁ ይገባልም ተብሏል።

የጎግል መረጃ እንደሚያመለክተው በዓለም ዙሪያ ከሚገኙት የአንድሮይድ ተጠቃሚዎች ውስጥ 42 ነጥብ 1 በመቶው የሚጠቀሙት አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም 6 ነጥብ 0 እና ከዚያ በቻች ነው።

ከአውሮፓውያኑ 2019 ጀምሮ ደግሞ ከአንድሮይድ 7 ነጥብ 0 በታች ላሉ ኦፕሬቲንግ ሲስተሞች ምንም አይነት የደህንነት ማዘመኛ እንዳልተደረገላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህም በዓለም ዙሪያ ካሉ 5 አንድሮይድ ስማርት ስልኮች ሁለቱ የደህንነት ማዘመኛ እንደማይደርሳቸው ነው የሚያመላክተው።

ስለዚህም የስማርት ስልካቸው አንድሮይድ ኦፕሬቲንግ ሲስተም ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ሰዎች ለቫይረስ እና መረጃ ጠላፊዎች ስለተጋለጡ ጥንቃቄ ቢያደርጉ መልካም ነውም ተብሏል።

ከጎግል ፕሌይ ስቶር ውጭ መተግበሪያዎችን ወደ ስልክ አለማውረድ፣ ምንጩ ላልታወቀ የጽሁፍ እና መልቲ ሚዲያ መልዕክቶች አለመክፈት እና ምላሽ አለመስጠት፣ በስልክ ላይ ያሉትን መረጃዎችን ቢያንስ ሁለት ቦታ ላይ እንደ መጠባበቂያ ማስቀመጥ እንዲሁም ፀረ ቫይረስ መተግበሪያዎችን መጫን ለጥንቃቄ የተቀመጡ ምክረ ሃሳቦች ናቸው።

ምንጭ፦ ቢቢሲ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.