Fana: At a Speed of Life!

ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እየተከናወነ ነው-ግብርና ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዘንድሮ የኅብረተሰብ ተሳትፎ ስራ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር የሚበልጥ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።
 
ሚኒስቴሩ በኦሮሚያ፣ አማራና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የተጀመረው የተፋሰስ ልማት ስራ በነገው ዕለት በደቡብ ክልል እንደሚጀመርም አስታውቋል።
 
በተያዘው ወር የመጀመሪያ ሣምንት የተጀመረው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ “የአየር ንብረት ለውጥንና ሠላማችንን በተባባረ ክንድ” በሚል መሪ ሃሳብ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።
 
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር ተፈራ ታደሰ እንደገለጹት፥ በየዓመቱ ጥር ወር ላይ የሚሰራው የተፈጥሮ ሃብት ስራ ከስልጠና ጀምሮ በቂ ዝግጅት ተደርጎበታል።
 
የተፈጥሮ ሃብት መመናመንና መራቆትን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችለው ተግባር በአብዛኛው የአገሪቷ አካባቢዎች እንደተጀመረም ገልጸዋል።
 
ከ2 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ከሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በተጨማሪ ቀድመው በተሰሩ በ1 ነጥብ 8 ሚሊየን ሄክታር መሬት የማደስ ስራ እንደሚተገበር ተናግረዋል።
 
የአፈርና ውሃ ጥበቃ እና የደን ተከላ ሥራዎች አገሪቷ ለአየር ንብረት ለውጥ አደጋ እንዳትጋለጥና የድርቅና የጎርፍ አደጋዎች እንዳይከሰቱ አስተዋጽኦው የጎላ ነው ብለዋል።
 
በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራው በየቀኑ ከ13 ሚሊየን የሚልቁ ዜጎች የሚሳተፉበት እንደሚሆን አቶ ተፈራ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
ኅብረተሰቡ በዘንድሮ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ በስፋት በመሳተፍ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝም ጥሪ አስተላልፈዋል።
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.