Fana: At a Speed of Life!

ከ300 በላይ የዱር እንስሳት በአንድነት ፓርክ ሊጎበኙ ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በአንድነት ፓርክ ከ300 በላይ ልዩ ልዩ የዱር እንስሳትን የያዘ ማሳያ በቅርቡ ለጉብኝት እንደሚከፈት ፓርኩ አስታወቀ።

ከዛሬ ጀምሮም በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚገኙ ጎብኚዎች ፓርኩን በክፍያ እንደሚጎበኙ የፓርኩ ስራ አስኪያጅ ዶክተር ታምራት ኃይሌ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል።

በታላቁ ቤተ መንግስት ቅጥር ግቢ የተገነባው የአንድነት ፓርክ የምሥራቅ አፍሪካ ሃገራት መሪዎችና ተጋባዦች በተገኙበት ባለፈው ወር መጨረሻ ተመርቆ ስራ መጀመሩ ይታወሳል።

ኢትዮጵያን በአንድ ስፍራ የሚያስተዋውቀው ይህ ፓርክ ከያዛቸው ዋና ዋና መስህቦች መካከል ብርቅየው ባለ ጥቁር ጎፈር አንበሳ፣ ሃገር በቀል ዕጽዋት፣ የክልሎች እልፍኝ፣ አረንጓዴ ስፍራ፣ ታሪካዊ ህንጻዎችና ዐውደ ርዕዮች እንዲሁም የእንስሳት ማቆያ ይጠቀሳሉ።

ፓርኩ ስራ ከጀመረ አንስቶ 17 ሺህ የሃገር ውስጥና የውጭ ሃገራት ጎብኚዎችን ያስተናገደ ሲሆን፥ 5 ሚሊየን ብር ገቢ መገኘቱንም ነው ስራ አስኪያጁ የተናገሩት።

በቅርቡም 46 አይነት ዝርያ ያላቸው 312 ልዩ ልዩ የዱር እንስሳት “የአንድነት የእንስሳት ማሳያ”ን ይቀላቀላሉ ብለዋል።

ከኢትዮጵያና ከሌሎችም የአፍሪካ ሃገራት ተሰባስበው ወደ ፓርኩ ከሚገቡት የተለየ ተፈጥሮና ባህርይ ካላቸው የዱር እንስሳት ባሻገር አዕዋፋትና አሳዎችም ይኖራሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.