Fana: At a Speed of Life!

ከ32 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ ሆነዋል – ዶክተር ሊያ ታደሰ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከ32 ሚሊየን በላይ ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ መሆናቸውን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደስ ገለፁ።

በአማራ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከልና የጤና መድህን ተደራሽነትን ለማረጋገጥ  የንቅናቄ ዘመቻ ወይይት እየተካሄደ ነው።

በውይይቱ የክልሉ ርዕስ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ፣የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ ሀላፊዎች እንዲሁም የዞንና የወረዳ አመራሮች ተገኝተዋል።

ዶክተር ሊያ ታደሰ በዚህ ወቅት ባደረጉት ንግግር  የጤና መድህን ስርአት በገጠርና በከተሞች መደበኛ ባልሆነው የኢኮኖሚ ዘርፍ ተሠማርተው ለሚገኙ ዜጎች ተጠቃሚነትን የሚረጋግጥ ስርአት ነው ብለዋል።

የሁሉን አቀፍ የጤና መድህን ሁለት ዋና ዋና አላማዎች እንዳለው የገለፁት ዶክተር ሊያ አንደኛው ከኪስ በሚወጣ ወጪ ለሚታከሙ  ዜጎች ለድህነት እንዳይጋለጡና አስፈላጊውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ  ለማድረግ ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

ሁለተኛው የጤና ስርዓት ዘላቂ የሆነ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው በማድረግ ትልቅ ሚና የሚጫወት ፕሮግራም ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል።

በሀገር ደረጃ በ2003 ዓ.ም በ13 ወረዳዎች ተጀመረው የጤና መድህን ስርዓት በ2012 ዓ.ም በ770 ወረዳዎች በትግበራ ላይ ሲሆን 32 ሚሊየን ዜጎች የጤና መድህን ሽፋን ተጠቃሚ መሆን ችለዋል ብለዋል ሚኒስትሯ።

ከአባላቱም 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን የተናገሩት ሚኒስትሯ 1 ነጥብ 6 ሚሊየን ዜጎች በጤና መድህኑ ወጪ ተሸፍኖላቸው የህክምና ጤና አገልግሎት  ማግኘት መቻላቸውን ጠቅሰዋል።

የጤና መድህኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ አባላት በማፍራት ያለው አፈፃፀም 82 በመቶ ሲሆን በአማራ ክልል ያለው አፈፃፀም ደግሞ 92 መሆኑን ገለፀዋል።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ  እንደ ሀገርና ክልል ስርጭቱ እና ወደ ፅኑ ህሙማን  የሚገቡ የኮሮቫይረስ ህሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን በመግለፅ ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ አበት ብለዋል።

የተቀዛቀዘውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የመከላከል ስራና የጤና መድህን ተደራሽነት ለማረጋገጥ ከጥር 1 እስከ 30 ቀን 2013 ዓ.ም የአንድ ወር የንቅናቄ ዘመቻ በአማራ ክልል እንደሚካሄድ የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ ተናግረዋል።

የክልሉ ርዕስ መስተደድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በኩላቸው ህብረተሰቡ በሠላም ማስከበር ያደረገውን የተቀናጀ ስራ የኮሮና ቫይረስን በመከላከልና የጤና መድህን ተደራሽነትን በማረጋገጥ ሊደግመው እንደሚገባው አስረድተዋል።

የክልሉ  መንግስት ከዚህ በፊት ሲያደርገው እንደነበረው ሁሉ አሁንም የኮሮና ቫይረስን የመከላከል እና የጤና መድህን ተደራሽነትን የማረጋገጥ ስራ አጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት።

በናትናኤል ጥጋቡ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.