Fana: At a Speed of Life!

ከ50 በመቶ በላይ እሴት የተጨመረባቸው ተሽከርካሪዎች ለውጪ ገበያ ቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ50 በመቶ በላይ እሴት የተጨመረባቸው እና በአዲሱ የንግድ ምልክት ወደ ገበያ የገቡ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ፍራንኮን በተባለው ድርጅት ለውጪ ገበያ ተላኩ፡፡
ፍራንኮን የተባለው ድርጅት ለ15ኛ ዙር ከባድ መኪናዎችን ለውጪ ገበያ ማቅረቡን በተመለከተ በወዳጅነት አደባባይ ባዘጋጀው ማሳያ ላይ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል÷ አምራቾች በስራቸው ጊዜ የሚያጋጥማቸውን መሰናክል ተቋቁመው በማለፍ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ፋይዳቸውን በማይናጋ መሰረት ላይ ለመጣል መስራት አለባቸው ብለዋል፡፡
አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሚገጥሟቸው ችግሮች እጅ መስጠት ሳይሆን÷ ለችግሮቹ የመፍትሔ ሀሳብ አፍላቂዎች መሆንና ያጋጠሙ ችግሮች ለስራ መሻሻልና ዕድገት ጠቃሚ ግብዓቶች አድርጎ በመውሰድ ጠንክሮ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡ ፍራንኮን የጀመረው ስራ ተስፋ ሰጭ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍራንችስኮ ቪሎኒ ድርጅቱ ከተቋቋመ 10 ዓመታትን ያሳለፈ መሆኑን ገልጸው÷ እስከ አሁን ከ15 በላይ የሚሆኑ መኪናዎችን ወደ ኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን እንዲሁም ወደ ኡጋንዳ ሀገራት ለውጪ ገበያ መላካቸውን አብራርተዋል፡፡
ፍራንኩን 60 በመቶ የሀገር ውስጥ ምርት በመጠቀም የመኪናዎችን የአካል ክፍል እንደሚያመርት የተናገሩት አቶ ፍራንችስኮ÷ ለሀገር ውስጥ ገበያ ከ200 በላይ ተሸከርካሪዎችን ሰርተው መሸጣቸውን እና በቀጣይም 67 የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን ለመሥራት ትዕዛዝ መቀበላቸውን አስረድተዋል፡፡
ድርጅቱ በሙሉ አቅሙ ወደ ስራ በሚገባበት ወቅትም ለ320 ዜጎች የስራ ዕድል ይፈጥራል መባሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.