Fana: At a Speed of Life!

ክልሎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 19 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ምክትል ርዕሳነ መሥተዳድሮች እና ከሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች ከንቲባዎች ጋር በኮሮና ቫይረስ የመከላከል ተግባራት ዙሪያ ተወያይተዋል።

በዚህ ወቅትም ሁሉም ክልሎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል አስፈላጊ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች መከናወናቸውን አስታውቀዋል።

የቫይረሱ የመከላከያ መንገዶችን በተመለከተ ክልል አቀፍ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እያስጀመሩ መሆኑም ተመላክቷል።

ይሁን እንጅ በሁሉም ስፍራ በተለይም በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አካላዊ ርቀትን ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በቪዲዮ ኮንፈረንሰ በተደረገው በዚህ ውይይት ክልሎች የህክምና መገልገያዎች እና መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲደረጉላቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

ከዚህ ባለፈም አንዳንድ ክልሎች የህክምና ባለሞያዎች እጥረት እንዳለባቸው ማሳወቃቸውን ከጠቅላይ ሚነስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል ክልሎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ያላቸውን ዝግጁነት በመግለጽ በጉዳዩ ዙሪያ አስፈላጊውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እያበረከቱ ለሚገኙ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሃብቶች፣ ግለሰቦች እና ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል።

“በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ የገለጣችሁት የደግነት ሥራችሁ፣ ብርታታችሁ እንዲሁም አዎንታዊ እና ገንቢ ተሳትፏችሁ በእጅጉ የሚመሰገን ነው፤ እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች መሆናችሁን አስመስክራችኋል” ብለዋል  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት የምስጋና መልዕክት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.