Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ለሚያደርገው ጥረት የሃረሪ ክልል እገዛ እንደሚያደርግ አስታወቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 8 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ብሄራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ለሚያደርገው ጥረት የሃረሪ ክልል እገዛ እንደሚያደርግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ።

የኮሚሽኑ አባላት በዛሬው ዕለት ከሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ ከክልሉ ካቢኔ አባላት እና ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ መንግስት በሃገሪቱ የጸጥታ መደፍረስ ችግሮች ተቀርፈውና ተቃርኖዎች በእርቅ ተፈተው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማሰብ ኮሚሽኑን ማቋቋሙ ወቅቱን የጠበቀና ተገቢነት ያለው መሆኑን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና የተጀመረው ሃገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረው ከማድረግ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።
በሚያደርገው እንቅስቃሴም የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በክልሉ ለዘመናት የቆየውን የሰላም፣ የመከባበርና የመቻቻል እንዲሁም በአብሮነት የመኖር እሴትን ለማስፋት በጋራ እንደሚሰሩ ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የክልሉ መንግስት በባለቤትነት መስራት የሚገባውን ስራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

የኮሚሽኑ ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ በሃገሪቱ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።

የኮሚሽኑ ዋና ዓላማ በሃገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ መስራት መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዚህም የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን ሚና ሊወጡ እንደሚገባ አውስተዋል።

ከጥንት ጀምሮ በህዝብ መካከል ችግር አለመኖሩን እና ችግሩ የስልጣን መሆኑን በመጥቀስ፥ ይህን ለትውልድ ማስተማር ይገባል ያሉት ደግሞ የኮሚሽኑ አባል ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ ናቸው።

መረጃው የሃረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ነው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.