Fana: At a Speed of Life!

ኮሚሽኑ የሁሉንም መንግስት ሰራተኞች  ሀብት ሊመዘግብ ነው

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 28 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን በ2013 በጀት ዓመት የሁሉንም መንግስት ሰራተኞች ሀብት ሊመዘግብ መሆኑን አስታወቀ።
 
ሀብትን ማሳወቅና ማስመዝገብ የመንግስት አሠራርን በግልጽነትና በተጠያቂነት ላይ ለመመስረት፣ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ኃላፊነትና የግል ጥቅም ሳይቀላቀሉ በየራሳቸው መንገድ የሚመሩበትን ግልጽ ሥርዓት በመዘርጋት ሊፈጠር የሚችለውን የጥቅም ግጭት ለማስወገድ ይረዳል ተብሏል።
 
ስለሆነም የሁሉንም የመንግስት ሰራተኞች ሀብት መመዝገብ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት እያደገ ከመጣው የመንግስት በጀትና ሀገራዊ ዕድገት ጋር የተጣጣመ የፀረ-ሙስና ትግል ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑ ተመላክቷል።
 
ከዚህም በተጨማሪ ኮሚሽኑ በሀብት ምዝገባው ዘርፍ ልምድ እየቀሰመና አቅሙን እያሳደገ በመምጣቱ የሀብት ምዝገባው ሥራ በተሟላ መንገድ ማስኬድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ መሆኑ ነው የተገለጸው።
 
ለዚህ ደግሞ የሀብት ምዝገባ ሥራ ዋነኛ ከሚባሉት የሙስናና ብልሹ አሰራሮች መከላከያ መንገዶች ውስጥ አንዱ ነው ተብሏል ።
 
ስለሆነም ኮሚሽኑ ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ ቀደም ሲል ሲመዘግብ ከነበረው የተሿሚዎችና የህዝብ ተመራጮች በተጨማሪ የሁሉንም መንግስት ሰራተኞች ሀብት ለመመዝገብ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁ ተገልጿል።
 
የምዝገባውን ሥርዓት የሚያስተባብረውና የሚያስፈጽመው ደግሞ በየተቋማቱ የተሰየሙዉ የሥነምግባር መኮንኑ ሲሆን÷ የእያንዳንዱ መንግስት ሰራተኛ ሀብት ምዝገባ የሚከናወነው ሰራተኛው በሚሰራበት ተቋም መሆኑም ነው የተገለጸው።
 
ይህንንም ስራ ለማከናወን የሚያስችል ሥልጠናም ከሐምሌ 14 እስከ 18 ቀን 2012 ዓ.ም ለ213 የሥነምግባር መኮንኖች መሰጠቱ ተገልጿል።
 
ከዚያም ባለፈ የሀብት ምዝገባውን ሥራ ይበልጥ የተሳለጠ ለማድረግ የሥራ ዋስትናን በማረጋገጥ፣ የህግ ማዕቀፎች በማዘጋጀት እንዲሁም የሀብት ምዝገባ ሥራውን በቴክኖሎጂ በማስደገፍ የሚሰራ ይሆናልም ነው የተባለው።
 
ኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ሥራ ከጀመረበት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ የ220 ሺህ ተሿሚዎች፣የህዝብ ተመራጮችና የተወሰኑ የመንግስት ሰራተኞችን ሀብት መመዝገቡን ከፌደራል የሥነ ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.