Fana: At a Speed of Life!

ኮሚቴው የተጓተቱ የመስኖ ፕሮጀክቶችን በአፋጣኝ ማጠናቀቅ እንደሚገባ አሳሰበ

አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 12 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንዳር፣ ምዕራብ እና ደቡብ ጎንደር ዞኖች በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ተመልክቷል፡፡
ምልከታ የተደረገባቸው የመገጭ፣ ርብ እና ሰራባ የመስኖ ፕሮጀክቶች ህብረተሰቡ ተስፋ የጣለባቸው ትልቅ ፕሮጀክቶች በመሆናቸው የክልሉ መንግስት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር ለችግሮቹ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንደሚገባው ቡድኑ አሳስቧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈትያ የሱፍ የመገጭ መስኖ ፕሮጀክት በ2005 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳልተጠናቀቀና ሌሎቹም የመስኖ ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜ መዘግየታቸው በበጀት ይሁን በህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ላይ የፈጠረው ጫና ከባድ በመሆኑ የህብረተሰቡን ቅሬታ መፍታት ይገባልምል ብለዋል፡፡
እንዲሁም የተቋራጮችን አቅም በማጎልበት፤ አስፈላጊ ግብአቶችን በማቅረብና ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በመስራት የፕሮጀክቶቹን ተፈጻሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው ÷ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተናበው በመስራት ለፕሮጀክቶቹ ተፈጻሚነት የበኩላቸውን እንዲወጡ እና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በኩል ተጨማሪ ማሽነሪዎችን በማቅረብ እንዲሁም አዲስ ቡድን በማቋቋም ለፕሮጀክቶቹ መጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋፅኦ እንደሚደርግ ገልፀዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም በሰራባ መስኖ ፓምፕ 4 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታስቦ የነበረ ቢሆንም በኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት 1 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ እያለማ በመሆኑ ይህን ችግር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመስራት ለመቅረፍና የህብረተሰቡን የግብርና አሰራሮች ለማዘመን እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡
የአማር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታሁን ማንደፍሮ የፕሮጀክቶቹ መጓትት መንግስት ለቃሉ ታማኝ እንዳይሆን ማድረጋቸውንና የህዝብን አመኔታ እያሳጣ በመሆኑ ለቀጣይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለችግሮቹ እልባት መስጠት ይገባዋል ብለዋል፡፡
የመገጭ የመስኖ ፕሮጀክት አማካሪ ተጠሪ መሃንዲስ ኢንጂነር ይርጋ አበባዬ ፕሮጀክቱ 68 ነጥብ 8 በመቶ መጠናቀቁን ጠቁመው በ2014 ህዳር ወር ላይ እንደሚጠናቀቅ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የአማራ ክልል ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ቢሮ ከፌደራል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር 14 የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕሮጀክት ለመገንባት የውል ስምምነት መፈራረሙን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.