Fana: At a Speed of Life!

ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) በተወለደ በ57 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

ዶክሌ በሚለው ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ወንድወሰን ብርሃኑ ባጋጠመው የልብ ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ትናንት በአሜሪካ ዋሽንግተን ሜድስታር ሆስፒታል ማረፉን የሙያ አጋሩ አርቲስት ቴዎድሮስ ለገሰ ገልጿል።

“ዶክሌ ቅንና ታዛዥ ባለሙያ ነበረ” ያለው አርቲስት ቴዎድሮስ÷ ኢትዮጵያውያን ኮሜዲያን ዶክሌን ሲረዱት ቢቆይም ለሁለተኛ ጊዜ ታሞ ሆስፒታል ገብቶ ህክምና እንዲያገኝ እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ህይወቱ አልፏል ብሏል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተወልዶ ያደገው ኮሜዲያን ዶክሌ በመድኃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል።

የእሱንም ሆነ የቤተሰቡን ህይወት ለመምራት በመካኒክነት ትምህርት ቀስሞ ሲሰራ የቆየ ሲሆን÷በኋላ ላይም የጥበቡን ዓለም በመቀላቀል በኮሜዲ ዘርፍ አንቱታን ያተረፈባቸውን በርካታ አይረሴ ስራዎችን ሰርቷል።

በስታንድ አፕ ኮሜዲ በርካታ አጫጭር ቁምነገር አዘል ቀልዶችን ያቀረበው ኮሜዲያን ዶክሌ÷ በሙሉ ጊዜ የፊልም ስራዎች ላይ በመሳተፍ ዕውቅና አትርፏል፡፡

ለአብነትም የራስ አሽከር የሚለው ታሪክ ቀመስ ፊልም ላይ የትወና ብቃቱን አስመስክሯል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በስራ አጋጣሚ ከስምንት ዓመታት በፊት ወደ አሜሪካ አቅንቶ ኑሮውን በዚያው አድርጎ የነበረው ኮሜዲያን ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ) ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ነበር።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.