Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከአውሮፓ ህብረት የውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 20፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ከአውሮፓ ህብረት የውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ይልቫ ጆሐንሰን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም ወይዘሮ ሙፈሪሃት ኢትዮጵያ እያደረገች ስላለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለኮሚሽነሯ ገለጻ ያደረጉላቸው ሲሆን፥ የአውሮፓ ህብረት ለውጡን በማበረታታትና በመደገፍ ያሳየውን አጋርነትም አድንቀዋል።

የኢትዮጵያና አውሮፓ ግንኙነት በሀገራት የጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ስለሆነ ትብብሩ ወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውን ከሰላም ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በአካባቢው ሰላምና መረጋገት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ እያበረከተች ያለውን አስተዋጽኦ በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አያይዘውም በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ በማስፈን ልማትን ለማረጋገጥ በሁሉም ዘርፎች ላይ የተጀመሩ ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።

ህገወጥ የሰዎች ዝውውር እንዲሁም ስደት የሚያስከትለውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በሚመለከት የተወያዩ ሲሆን፥ ኢትዮጵያ ችግሩን ለመቀነስ የምትከተለውን ቀጣይ የለውጥ አቅጣጫና ተግዳሮቶችን አስመልክተው ለኮሚሽነሯ ገለጻ አድርገውላቸዋል።

የአውሮፓ ህብረት የውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽነር ይልቫ ጆሐንሰን በበኩላቸው፥ ስደትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባይቻል እንኳን በሀገራት ላይ የሚያሳርፈውን ማህበራዊ ተጽዕኖ በትብብር ከተሰራ መቀነስ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.