Fana: At a Speed of Life!

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከከተማዋ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት ጋር ተወያዩ።

በዚህ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የላዳ ታክሲ ባለንብረቶች ማህበራት ጥያቄ አግባብነት ያለው እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት እንደሚፈታው ምክትል ከንቲባዋ ተናግረዋል።

ማህበራቱም እድሜ ጠገብ የከተማ የላዳ ታክሲዎች ከተማዋን በሚመጥን አዳዲስ ዘመናዊ ታክሲዎች ተቀይረው መስራት እንዲችሉ ብድር እንዲመቻች፣ ህገ ወጥ አገልግሎች ሰጭዎች ህጋዊ ሆነው መወዳደር እንዲችሉ ይደረግ ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።

ምክትል ከንቲባዋም ማህበራቱ ዘመናዊ በመሆን የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ፣ በህጋዊ መንገድ እንዲያገለግሉ፣ ህግና ስርአትን በጠበቀ መልኩ እንዲሰሩ እና ለዚህም ሁኔታዎች ይመቻቹ በሚል ያቀረቡት ጥያቄ አግባብነት ያለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በመንግስት በኩል ችግሮቹን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ማለታቸውንም ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ከጥያቄያቸው በመነሳት አዳዲስ ታክሲዎችን ማስገባት እንዲችሉ ከቀረጥ ነፃ አገልግሎት ተመቻችቶላቸዋል።

በተጨማሪም የብድር አገልግሎት በንግድ ባንክ በኩል የታመነበት ጉዳይ በመሆኑ ተደራጅተው መጠቀም የሚችሉ መሆኑንም አንስተዋል።

የዘመናዊ የታክሲ አገልግሎት ከተማዋን በማዘመን በኩል ትልቅ ፋይዳ ያለው መሆኑን በመጥቀስም፥ የታክሲ ማህበራቱም ተደራጅተው ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለመጠበቅ የራሳቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.