Fana: At a Speed of Life!

ወጥነት ያለው ሀገር አቀፍ የፖሊስ ስታንዳርድ ለማህበረሰቡ ለማቅረብ የፖሊስ አመራሮች ሃላፊነታችውን ሊወጡ ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ዘመናዊና ዘመን ተሻጋሪ የፖሊስ ተቋም ለመገንባት ከፌደራል፣ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽን ለተውጣጡ የፖሊስ አመራሮች ስልጠና እየተሰጠ ነው።
ለአራት ቀናት የሚቆየው ስልጠና በፖሊስ ዶክትሪን፣ በሰራዊቱ የለውጥ አመራር፣ በፖሊስ ስነ-ምግባርና ስብዕና ዙሪያ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል እንዳሻው ጣሰው ስልጠናው የፖሊስ የመፈጸም አቅምን ከመጨመር ባለፈ ፖሊስ በስነ-ምግባር ሁሉንም ዜጎች በእኩል ማገልገል እንዲችል እየተሰሩ ያሉ የለውጥ ተግባራትን ለመደገፍ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
አያይዘውም ባለፉት ሁለት አመታት የፖሊስ ስራ ፈታኝ እንደነበር ጠቅሰው በህዝብና መንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ ለመፈጸም ፖሊስ ራሱን በማጠናከርና በማጥራት ሰላም ፈላጊውን ህዝብ ያሳተፈ ስራ መስራት አለበት ብለዋል ።
ዘመኑን የሚመጥን፣ ወጥነት ያለው ሀገር አቀፍ የፖሊስ ስታንዳርድ ለማህበረሰቡ ማቅረብ እንዲቻልም ከሁሉም ፖሊስ ኮሚሽን የተውጣጡ የፖሊስ አመራሮች ስልጠናውን በሚገባ በመረዳትና ተግባራዊ ማድረግ ይገባቸዋልም ነው ያሉት፡፡
ከዚህ ባለፈም በስልጠናው የተገኘውን እውቀት ለሁሉም የፖሊስ አባላት እንዲዳረስ ሃላፊነታችውን እንዲወጡ ኮሚሽነር ጄነራሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.