Fana: At a Speed of Life!

ውስጣችንን፣ አካባቢያችንንና ሀገራችንን ሰላማዊ ለማድረግ እያንዳንዳችን ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅብናል – አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ውስጣችንን፣ አካባቢያችንንና ሀገራችንን ብሎም ዓለማችንን ሰላማዊ ለማድረግ የእያንዳንዳችን ድርሻ የማይናቅ ሚና ስለሚጫወት ለሰላም ቅድሚያ መስጠት ይጠበቅብናል ሲሉ አቶ አወል አወል አርባ መልዕክት አስተላለፉ።

የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ 1443ኛ የኢድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በመልዕክታቸው፥ በየትኛውም ጫፍ ችግር ቢያጋጥም ችግሩን በማባባስ ሳይሆን ችግሩን አላህ በሚወደው መንገድ በሰከነ አእምሮ በቅንነት በመፍታት መረባረብ ማገዝ ይጠበቅብናል ሲሉም አሰገንዝበዋል።

አቶ አወል አርባ እንደገለጹት፥ ህዝብን ከተረጋጋ ኑሮው በማፈናቀል፣ በመግደል እና በማሳደድ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት የሚያደርጉትን መሯሯጥ በጋራ በመሆን መግታት ግድ ይላል።
በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ኢ-ፍትሀዊና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በማንም ይፈፀም በማንም ሊወገዝ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

ፀረ-ሰላም የሆነው ጁንታ ለሰላም አልገዛም ብሎ ወረራ ባካሄደበት ወቅት ለሰላም ሲሉ የተዋደቁ ጀግኖች በኢድ ቀን በክብር እናስታውሳቸዋለን ብለዋል።

“ለሰላም ሲሉ መስዋእት የሆኑትን ጀግኖች አላህ የጀነት ሰው ይበላቸው” ያሉት አቶ አወል፥ የነዚህን ጀግኖች ልጆች፣ ባለቤቶች እንዲሁም ዘመዶቻቸውን ማሰብና መንከባከብ እንደሚገባ ገልጸው፥ ለሰላም ሲሉ ለከፈሉት ተጋድሎ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል ነው ያሉት።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ፣ በመጠየቅ በመዘየር ማሳለፋችን በየዕለቱ ስናፈጥር ደስታችን ወደር አልነበረውም ብለዋል።

በዚህ የደስታ ቀን ደስታችንን እጥፍ ድርብ ከሚያደርጉት አንዱና ዋነኛው ሌሎች ላይ ደስታን በመፍጠር የምናገኘው ደስታ በመሆኑ ቀኑን የላቀ እንደሚያደርገውም አብራርተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ያስተላለፉት መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በቅድሚያ እንኳን ለ1443 ሂጅራ የዒድ አል ፈጥር በዓል አደረሰን!
አላሁ አክበር! አላሁ አክበር! አላሁ አክበር ! ላኢላሃ ኢለላህ አላሁ አክበር ወሊላሂል ሃምድ

ታላቁ የኢባዳ፣ የመተዛዘን እና የአብሮነት ወር ረመዷን መጠናቀቅን ተከትሎ ወርሃ ሸዋል አንድ ሲል በፆም በፀሎት ወሩን ያሳለፉ ምዕመናን ኢድ አል ፈጥር በዓልን በደስታ እና የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ ዘካተል ፊጥር በማውጣት በደስታ ያሳልፉታል።

ከዒድ ጋር በተያያዘ ዘካተል ፊጥርን መስጠት መታዘዙ የተለያዩ ችግረኞችን ማስታወስ እና አቅም በፈቀደ መጠን ችግራቸውን ለመቅረፍ ጥረት ማድረግ የሚደገፍ ተግባር መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡

የኢስላም ሊቃውንት ስለ ዒድ ሲናገሩ ዒድ የተባለበት ምክንያት ዒድ በየአመቱ አዲስ ደስታን ይዞ የሚመለስ ከመሆኑ አንፃር መሆኑን እና ‹‹ዓደ›› (ተመለሰ) ከሚለው ቃል የተወሰደ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ በዚህ የደስታ ቀን ደስታችንን እጥፍ ድርብ ከሚያደርጉት አንዱና ዋነኛው በራስ ደስታ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ላይ ደስታን በመፍጠር የምናገኘው ደስታ በመሆኑ ቀኑን የላቀ ያደርገዋል።

በረመዳን በተለይም ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ፣ በመጠየቅ በመዘየር ማሳለፋችን በየዕለቱ ስናፈጥር ደስታችን ወደር አልነበረውም፣ በኢድ ወሳኝ ቀንም በተለየ ሁኔታ የተቸገሩ ወገኖችን ለችግራቸው በመድረስ በየዕለቱ ኢፍጧር ሰአት ያገኘነው ደስታና እርካታ በወሩ ኢፍጧርም በመድገም አብሮነታችን በተግባር ማሳየት ይገባል። ይህን ደስታም በተለየ ሁኔታ ትኩረት አድርገን በጁንታው ወረራ የተፈናቀሉ ወገኖች ጋር ኢድን በማሳለፍ እነሱን በማገዝ ዒዱን ያማረ ማድረግ አለብን።

በረመዳን የታየው ወደ መልካም ነገር መሽቀዳደም፣ ኸይርን ስራ አዘውትሮ መፈፀም በሌላ ወራት የሚቋረጥ ሳይሆን ረመዳንን እንደ ትምህርት ቤት በመቁጠር ለቀጣይ ህይወታችን ስንቅ የምንሰንቅበት፣ መልካምን በመስራት፣ ከመጥፎ ተግባራት በመራቅ የተስተካከለና በስነ-ምግባር የታነፀ ህብረተሰብ መሆን ይጠበቃል።

ከነዚህ መልካም ተግባራት አንዱ ስለ ሰላም መስራት፣ ወደ ሰላም ጥሪ ማድረግ፣ ሰላምን መኖር ይጠቀሳል። ሰላም ለሁሉም ነገር ዋናኛ መሰረት በመሆኑ ሁላችንም በየአካባቢያችን የሰላም ባንዲራን ልናውለበልብ ይገባል። ሰላምን ለማደፍረስ ሴራ የሚያሴሩ፣ ህዝብን ከተረጋጋ ኑሮው በማፈናቀል፣ በመግደል እና በማሳደድ ርካሽ የፖለቲካ ትርፍን ለማግኘት የሚያደርጉትን መሯሯጥ በጋራ በመሆን መግታት ግድ ይላል።

በሀገራችን በየትኛውም አካባቢ የሚከሰቱ ኢ-ፍትሀዊና ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች በማንም ይፈፀም በማንም ሊወገዝ እና ጥፋተኞች በጥፋታቸው ልክ ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል።

ይሁንና በየትኛውም ጫፍ ችግር ቢያጋጥም ችግሩን በማባባስ ሳይሆን ችግሩን አላህ በሚወደው መንገድ በሰከነ አእምሮ በቅንነት በመፍታት መረባረብ ማገዝ ይጠበቅብናል ። እሳት ላይ ቤንዝን ማርከፍከፍ ጀግንነት ባለመሆኑ ለጠላቶቻችን በር መክፈት እና የበለጠ ለአደጋ ተጋላጭ ከመሆን ያለፈ ትርፍ አያስገኝልንም።

ሰላም ከሌላ ሃይማኖትን በአግባቡ መከወን ይከብዳል፣ ሰላም ከሌለ ስለ ብልፅግና ማውራት ይከብዳል፣ ሰላም በአካባቢያችን በውስጣችን ከታጣ ሁሉ ነገር ይቃወሳል፤ በመሆኑም ውስጣችንን፣ አካባቢያችንና ሀገራችንን ብሎም አለማችንን ሰላማዊ ለማድረግ የእያንዳንዳችን ድርሻ የማይናቅ ሚና ስለሚጫወት ቅድሚያ ለሰላም መስጠት ይጠበቅብናል።

ፀረ-ሰላም የሆነው ጁንታው ለሰላም አልገዛም ብሎ ወረራ ባካሄደበት ወቅትም ለሰላም ሲሉ የተዋደቁ ጀግኖች በዚህ በኢድ ቀን በክብር እናስታውሳቸዋለን፣ ለሰላም ሲሉ መስዋእት የሆኑትን አላህ የጀነት ሰው ይበላቸው፣ ከነዚህ ጀግኖች የቀሩ ልጆቻቸው፣ ባለቤቶቻቸው እንዲሁም ዘመዶቻቸውን ማሰብ፣ መንከባከብና ለሰላም ሲሉ ለከፈሉት ተጋድሎ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል።

በድጋሚ እንኳን ለ 1443 ሂጅራ ኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳቹህ አደረሰን እያልኩኝ ዒዱ የሰላም፣የፍቅርና የመተሳሰብ እንዲሆንላችሁ እመኛለሁ።

ኢድ ሙባረክ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.