Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ላይ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሚሊየን አለፈ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዓለም ላይ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሚሊየን አልፏል።

ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ደግሞ በአሜሪካና በአውሮፓ አዳዲስ በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ክብረወሰን በሆነ መጠን እየጨመረ ይገኛል ተብሏል።

በቫይረሱ ከተያዙ 50 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን በላይ ሰዎች ህይወታቸውን እንዳጡ የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያመላክታል፡፡

ይህ ቁጥር ምናልባትም በአንዳንድ ሃገራት ካለው የመመርመር አቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የሟቾቹ ቁጥር ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ነው የተነገረው።

ወረርሽኙ ከጠናባት አውሮፓ በቫይረሱ ከተያዙባት ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ 305 ሺህ 700 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በአሜሪካ ደግሞ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ወደ 10 ሚሊየን እየተጠጋ ሲሆን፥ 237 ሺህ 572 ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ነው የተሰማው።

በአሜሪካ ላለፉት ሦስት ቀናት በተከታታይ በየዕለቱ ከ125 ሺህ ሰዎች በላይ በወረርሽኙ እየተያዙ ነው ተብሏል።

ከሳምንት በፊት እገዳ ባስተላለፈችው ፈረንሳይ ቅዳሜ ዕለት ብቻ ከ86 ሺህ ሰው በላይ የተያዘ ሲሆን፥ ይህ ቁጥር ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛው መሆኑ ነው የተነገረው።

ብዙ ህዝብ በያዘችው ህንድ እንዲሁም ብራዚል በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ይገኛል።

በብራዚል ከ5 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ሰዎች ሲያዙ 162 ሺህ 397 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።

ብራዚል በዓለም ላይ በወረርሽኙ አማካኝነት ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን ያጡባት ሃገር ሆናለች።

በህንድ ደግሞ ከአሜሪካ በመቀጠል ከ8 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል።

ከእነዚህ መካከልም 126 ሺህ 611 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

በጥቅሉ ዓለም ላይ በወረርሽኙ ከተያዙት ከ50 ሚሊየን ሰዎች ውስጥ ከ35 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት ማገገማቸውን ነው መረጃዎች የሚያመላክቱት።

ምንጭ፡-ቢቢሲ

በአብርሃም ፈቀደ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.