Fana: At a Speed of Life!

ዓለም ላይ የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ከ10 አመታት በኋላ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ዓለም ላይ የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ በከፍተኛ ፍጥነት መጨመሩን አስታወቀ፡፡

ድርጅቱ ያወጣው መረጃ ዓለም ላይ ወርሃዊ የምግብ ሸቀጦች ዋጋ ከ10 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ያመላክታል፡፡

ጭማሪው ለ12 ወራት የታየ ሲሆን፥ ይህም ከፈረንጆቹ 2010/11 በኋላ ከፍተኛ ሆኖ ተመዝግቧልም ነው ያለው፡፡

ድርጅቱ ለመሰረታዊ የምግብ ፍጆታነት በሚውሉ የእህል አይነቶች፣ በወተት ተዋጽኦዎች፣ በቅባት እህሎች፣ ስጋ እና በስኳር ምርቶች ላይ ባደረገው ጥናት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አስታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም የምግብ ሸቀጦች በግንቦት ወር የ39 ነጥብ 7 በመቶ ጭማሪ ያሳዩ ሲሆን፥ ይህም ከፈረንጆቹ 2010 ጥቅምት ወር ወዲህ ከፍተኛው ወርሃዊ ጭማሪ መሆኑን አመላክቷል፡፡

በዋናነት ለዋጋ ጭማሪው በአትክልት ዘይቶች፣ ጥራጥሬና ስኳር የታየው ጭማሪ ምክንያት መሆኑንም ነው የድርጅቱ መረጃ የሚያመላክተው፡፡

ከዚህ ባለፈም የምርት እጥረትን ተከትሎ የተከሰተው የፍላጎትና የአቅርቦት አለመጣጣም ሌላው ምክንያት መሆኑንም ድርጅቱ የገለጸው፡፡

በተለይም በአንዳንድ ሃገራት ከኮቪድ19 ጋር ተያይዞ የወጣው የእንቅስቃሴ ክልከላ ድንጋጌ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረት በመፍጠር ለዋጋ ጭማሪ ማሻቀብ ምክንያት መሆኑንም ጠቅሷል፡፡

የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ደግሞ አሁን ካለው ጭማሪ ባሻገር የሚታየው የምርት አቅርቦት እጥረትና የፍላጎት መጨመር አለመጣጣም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበትን እንደሚያስከትል ያስጠነቅቃሉ፡፡

ምንጭ፦ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.