Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት እንዲያወግዝ ጥሪ ቀረበ

 

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 10፣2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት ለዳግም ጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅት በግልጽ እንዲያወግዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ኢትዮጵያ ለሰላም ያላትን ፅኑ አቋም በተግባራዊ እርምጃዎቿ እያሳየች መሆኗን ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘበው የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይም ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን መቋቋሙ፣ ሰብዓዊ ዓላማ ያለው የተኩስ ማቆም መደረጉ፣ ሰብዓዊ እርዳታዎች ወደ ትግራይ ክልል እንዲገቡ በመንግስት በኩል የተወሰዱ እርምጃዎችን በዚህ ረገድ በአብነት አንስተዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴጎን ኦባሳንጆ፣ ከአሜሪካ ልዩ መልዕክተኞችና ሌሎችም ዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ ጋር በሰላም ጉዳይ ላይ ውይይቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል።

መንግስት አሁንም ለሰላም ያለውን አቋም የሚያሳዩ ግልፅ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን ለተለያዩ የዓለም ማህበረሰብ አካላት የማስረዳቱ ስራ ቀጥሏል ነው ያሉት።

ሆኖም ኢትዮጵያ ለሰላም በርካታ ርቀቶችን ብትጓዝም አሸባሪው ህወሓት ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል።

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህንን የህወሓት የዳግም ጦርነት ዝግጅትና የታጣቂ ምልመላ በትክክል ተገንዝቦ በቡድኑ ላይ ጉልህ ተፅዕኖ እንዲያሳርፍ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በመሆኑም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት ለጦርነት የሚያደርገውን ዝግጅትና የአስገዳጅ የታጣቂ ምልምላ እንዲያቆም በጠንካራ አቋም ሊያወግዘው ይገባል ነው ያሉት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.