Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ጎን ሊቆም ይገባል – ቢለኔ ስዩም

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 27 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢለኔ ስዩም ከፎክስ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪው ህወሓት ኢኮኖሚውን፣ ፖለቲካውን እና መከላከያ ኃይሉን ተቆጣጥሮ የቆየ አምባገነን እና ጨፍጫፊ ቡድን እንደነበር አስታውሰዋል።

ይህ ቡድን በህዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የሥልጣን ጥሙ አገርሽቶበት እንደገና ወደ ሥልጣን ለመምጣት ጦርነት ጀምሯል ያሉት ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፥ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግን የትግራይን ህዝብ ለመጥቀም እየሰራሁ ነው እንደሚል ነው የተናገሩት።

ከዚህ በተቃራኒው ግን ኢትዮጵያ ላለፉት 30 ዓመታት ለገባችባቸው ጦርነቶች ምክንያቱ አሸባሪው ህወሓት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው አንስተዋል።

አያይዘውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሸባሪው ህወሓት ወደ ጅቡቲ እና ወደ አዲስ አበባ ለመስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ለመግታት ኢትጵያውያን እንዲዘምቱ ጥሪ አቅርበዋልም ነው ያሉት።

ጋዜጠኛዋ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ በኩል አንድነትን ለማስፈን እሰራለሁ ይላሉ፤ በሌላ በኩል ግን ኢትጵያ እየፈረሰች ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚፈልጉት ይሄን ነው ወይ፤ ወይስ ይህን አስከፊ ጦርነት ለማስቆም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን እያፈላለጉ ነው?” የሚል ጥያቄ አቅርባለች።

ቢለኔ ስዩም በሰጡት ምላሽም ኢትዮጵያ እየፈረሰች ነው የሚለው ፍረጃ ትክክል አለመሆኑን እና ጦርነቱ እየተካሄደ ያለው በአገሪቷ ሰሜን ክፍል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም አሸባሪው ቡድን ካወጀው ጦርነት ዜጎችን ለመጠበቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑንም አስረድተዋል፤ በትክክልም አንድነትን በኢትዮጵያ ለማረጋገጥ እየሠሩ ይገኛሉም ነውያሉት።

ላለፉት ሶስት ዓመታትም ለቡድኑ የሠላም ጥሪ ሲደረግ መቆየቱንም በምላሻቸው አስታውሰዋል።

አያይዘውም አሁን ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በጦር ግንባር እንደሚገኙና ግንባር ሆነው አመራር እየሰጡ መሆኑንም ገልጸዋል።

አሸባሪው ቡድን እየደከመና እየተሸነፈ ነው፤ ተዋጊዎቹም እየሸሹ እና እጃቸውን እየሰጡ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በጣም ሠፊ የህዝብ ተቀባይነት አላቸውም ነው ያሉት በምላሻቸው።

እሳቸው በግንባር ሆነው እየመሩት ያለው ዘመቻም አሸባሪው ህወሓት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ተደምስሶ ከእንግዲህ የኢትጵያ ስጋት መሆን እንዳይችል ለማድረግ ያለመ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት ከአንድ ወገን ባደረገው ተኩስ አቁም መከላከያ ኃይሉን ከትግራይ ክልል እንዳስወጣ ገለጸው፥ መንግስት እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ሲሸፍን እንደነበረም አውስተዋል።

የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቱ ለተጎዱ ወገኖች እንዳይደርስ ግን ህወሓት መሰናክል ሆኖ መቆየቱን ነው የገለጹት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠላም ለማስፈን የሚያደርጉት ጥረት ይሳካላቸዋል ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽም፥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሠላምንና አንድነትን ለማስፈን እንደሚሰሩ በመግለጽ የሚወራው የህወሓት የሃሰት ወሬ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሠላምን ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰሩ እና የመከላከያ ሰራዊቱን በግንባር እየመሩ የሚገኙ የአገር መሪ ናቸው ያሉት ቢለኔ ስዩም፥ ይህ ለአሸባሪው ራስ ምታት መሆኑንም ጠቁመዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ከህዝቦቿ በላይ ለኢትዮጵያ የሚያስብ እንደሌለ በመጥቀስም፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸጋሪውን ወቅት እንደምንሻገረው አውቆ ከኢትዮጵያ እና በህገ መንግስታዊ ምርጫ ከተመረጠው መንግስት ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል።

አካባቢዎን ይጠብቁ!
ወደ ግንባር ይዝመቱ!
መከላከያን ይደግፉ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.