Fana: At a Speed of Life!

ዘለፋ የበዛበት የዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን የፊት ለፊት ክርክር ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 20 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና የቀደሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለህዳሩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ንጋት ላይ የፊት ለፊት ክርክር አድርገዋል።

ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን በህዳር ወር የሚካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማሸነፍ ቅስቀሳዎችን ማድረግ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ሌሊት ላይም ዘለፋ የበዛበት እና አስደሳች አልነበረም የተባለውን የመጀመሪያ ክርክራቸውን አካሂደዋል።

ለ90 ደቂቃዎች በተካሄደው ክርክር ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ የነጭ የበላይነት፣ የጤና መድህን እና የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የክርክራቸው ማጠንጠኛ ነበር።

በዚህ ክርክር ላይ ጆ ባይደን ሃሳባቸውን ሲሰነዝሩ ዶናልድ ትራምፕ በተደጋጋሚ ሲያቆርጧቸው የታየ ሲሆን ጆ ባይደንም ለዶናልድ ትራምፕ ቀልደኛ እና አፍህን ዝጋ የሚሉ ቃላትን በመጠቀም ምላሽ ሲሰጡ ታይተዋል።

ነጩን ቤተ መንግስት ከተረከቡ ሊሰሯቸው ስለሚችሉ ጉዳዮች በተወሰነ ደረጃ ክርክር እና ውይይት ያደረጉት ዶናልድ ትራምፕ እና ጆ ባይደን ወሳኝ የሚባሉ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ክርክር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ነው የተባለው፡፡

የክርክሩ መሪ የነበረው የፎክስ ኒውሱ ክሪስ ዋላስ ትራምፕን የነጭ የበላይነትን ያወግዛሉ ወይ በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ መጀመሪያ ላይ ሊያወግዙ እንደሚችሉ ቢጠቅሱም የአክራሪ ነጮች ቡድን ስም ሲጠቀስ ጥቄውን ዘለውታል።

የምርጫውን ውጤት በፀጋ ከመቀበል ጋር በተያያዘ ለቀረበው ጥያቄም ፕሬዚዳንቱ “ምርጫው ሊጭበረበር ይችላል የሚል ግምት አለኝ” ብለዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞም ደጋፊዎቻቸው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዲሄዱ እና ነገሮችን በጥንቃቄ እንዲመለከቱም ጠይቀዋል።

ጆ ባይደን ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ በነበረው ክርክር ትራምፕ 200 ሺህ አሜሪካውያንን ከገደለው የኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ፍርሃት ላይ ናቸው ብለዋል።

ትራምፕ የበለጠ ካልፈጠኑ እና ብልህ ካልሆኑ በርካቶች አሁምን በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን ሊያጡ ይችላሉም ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ቃል የገቡትን የጤና መድህን ጉዳይም ዘንግተውታል በሚል ትችት ሰንዝረዋል፡፡

በአንጻሩ ትራምፕ “እኔ ስለሆንኩ እንጅ ባይደን ቢሆን የኮሮና ቫይረስ ጉዳት ከዚህ በባሰ ነበር” ሲሉ የተሻለ እርምጃ እንደወሰዱ ለማስረዳት ሞክረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ትራምፕ ባይደን በ47 አመት የፖለቲካ ቆይታቸው ምንም ያልሰሩና ይህንምም የአሜሪካ ህዝብ የሚያውቀው ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ተችተዋቸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ሰነፍ ተማሪ ነበርክ በማለት ወርፈዋቸዋል፡፡

ከታቀደው አውድ ውጭ ነበር በተባለለት ክርክር የተሻለው ማን እንደነበር ባይጠቀስም ትራምፕ የባይደንን ንግግር በተደጋጋሚ በማቋረጥ የበላይነታቸውን ለማሳየት ሞክረዋል ነው የተባለው፡፡

በተካሄደ የቅድመ ምርጫ ዳሰሳ ጆ ባይደን የተወሰነ ብልጫ አላቸው ቢባብልም በምርጫ ሂደት ወሳኝ በሚባሉ የአሜሪካ ግዛቶች ያለው ልዩነት ጠባብ ሊሆን እንደሚችል ነው እየተነገረ የሚገኘው።

ሁለተኛው ዙር ክርክር በቀጣዩ ሳምንት በምክትሎቻቸው አማካኝነት የሚካሄድ ይሆናል፡፡

ምንጭ፥ ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.