Fana: At a Speed of Life!

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል ሲሉ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡
ፕሬዚዳንቷ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፥ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ማቋቋምያ አዋጅን ባለፈው ሳምንት መፈረማቸውን አስታውቀዋል።
መፈረም ኃላፊነቴ ቢሆንም የእውነተኛና አካታች ብሔራዊ ምክክርን ቁልፍነት ስለማውቅ፣ ስለሠራሁበት፣ ውጤቱንም ስላየሁ አምንበታለሁ ነው ያሉት፡፡
እንደዚህ ያለ ምክክር በመሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲኖር ያደርጋል፣ ሃሳብን በግድ መጫንን፣ ጦር መማዘዝን፣ ሕዝብንና አገርን አደጋ ላይ መጣልን ከመሳሰሉ አደጋዎች እንደሚያድንም ተናግርዋል፡፡
“የንግግር፣ የመደማመጥ፣ የመከባበር አዲስ ባህል ይፈጥራል፣ እንደ እኛ ከአውዳሚ ጦርነት ማግስት ለሚገኝ አገር ጠቀሜታው ግልጽ ነው” ብለዋል።
ይህንን አገራዊ ምክክር እንዲመራና እንዲያካሂድ የሚቋቋመው ኮሚሽን አባላት ጥቆማ ሲካሄድ መቆየቱን በማንሳት፥ ለአንድ ሳምንት ከተራዘመ በኋላ ጥር 13 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚያበቃም ጠቁመዋል።
“ለኮሚሽነርነት የተጠቆሙ ሴቶች ቁጥር አነስተኛ ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ፣ ሴቶች መጠቆም አለባቸው፣ ያካሄድነው ጦርነት ያስከተለው ሰቆቃ የሴት መልክ ነው ያለው̏ ብለዋል፡፡
“በመቀሌ እና በደሴ መጠለያ ጣቢያዎች ያነጋገርኳቸው ሴቶች ገጽታ ይህንኑ ያረጋግጣል” ነው ያሉት፡፡
ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በመልዕክታቸው እንዚህ ሴቶች “ምንም እንኳን እያዘኑና እያለቀሱ ቢያነጋግሩኝም እንባቸውን ጠርገው ጥያቄ አቅርበዋልም ፣ የመፍትሄ ሃሳብም ሰጥተዋል” ብለዋል፡፡
ጦርነቱ በሴቶች ላይ ያስከተለው ሁኔታ ገና በብዙ የሚታይ ነው፤ ሴት ሰለባ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ አካል መሆንዋ ከግንዛቤ መወሰድ አለበት ያሉት ፕሬዚዳንቷ፥ የሴት ኮሚሽነሮች መኖር ካላቸው አጠቃላይ ኃላፊነት ጋር የእነዚህም ሴቶች ድምጽ ይሆናሉ ሲሉ አክለዋል፡፡
ስለሆነም በቀረው ጠባብ ጊዜ የወጡትን መስፈርቶች የሚያሟሉ ሴቶችን ህብረተሰቡ እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.