Fana: At a Speed of Life!

የሀገር መከላከያ ሰራዊት እያካሄደ ላለው ህግ የማስከበር ስራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የድሬዳዋ ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 4፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሀገር መከላከያ ሰራዊት የህግ የበላይነትን በማስከበር ሰላምን ለማስፈን እያከናወነ ላለው ተግባር ድጋፍ እንደሚያደርጉ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ነዋሪዎቹ ህግ በማስከበር ግዳጅ ላይ ለሚገኘው መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ ትላንት “ደሜን ለመከላከያ ሠራዊት” በሚል ደም ለግሰዋል።
“የህወሃት ሀገር አፍራሹ ቡድን በሰሜን እዝ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ተግባር ሰይጣናዊና የሚወገዝ ነው” ሲሉም ገልጸውታል ።
እንዲሁም ሠራዊቱ የህወሓትን ሽብርተኛ ቡድን ለህግ ለማቅረብና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለው እርምጃ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
“ድርድር የሚባል ነገር አያስፈልግም ፤ ቡድኑን ለህግ ተጠያቂ ማድረግና ሰላምን ማስፈን ይገባልም” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
“ላለፈው 27 ዓመት ዜጎችን በኃይማኖትና በብሔር ሲያጋጭና ሲገድል የነበረው የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ተግባር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያወግዘው ይገባል” ሲሉም ተናግረዋል።
“ሠራዊቱ የሀገር ሰላምና ህገ-መንግስታዊ ሰርዓቱን ለማስከበር የጀመረው ዘመቻ እንዲሳካ ደም መለገስ ብቻ ሣይሆን በገንዘብና በጉልበታችን ከጎኑ ለመቆም ተዘጋጅተናል” ነው ያሉት።
የመከላከያ ሠራዊቱ ሽብርተኛውን የህውሃት ቡድን ለመደምሰስ የጀመረው ተግባር በምንም መንገድ ወደ ኃላ መመለስ እንደሌለበት አስታውቀዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዩሱፍ ሰኢድ በበኩላቸው “አሸባሪውን የህወሃት ቡድን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተጀመረው ተግባር በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሁሉም ዜጋ ድጋፍ ያስፈልጋል” ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.