Fana: At a Speed of Life!

የሃገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹ ዕድል እንደሚፈጥሩ ም/ጠ/ ሚ አቶ ደመቀ ገለፁ

አዲስ አበባ፣ ጥር 12፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሃገር-በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹ ዕድል እንደሚፈጥሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልፀዋል።
 
በለንደን የተካሄደውን የብሪታኒያ – አፍሪካ ኢንቨስትመንት ጉባኤን አስመልክቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ የተጀመሩ የማሻሻያ እርምጃዎች የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በስፋት ለመሳብ እንደሚያግዙ ተናግረዋል።
 
የማሻሻያ እርምጃዎቹ ከሃገሪቱ የለውጥ ጉዞ ባህሪ ጋር ተገናዝበው የሚወሰዱ በመሆናቸው፤ በኢንቨስትመንት እና በንግድ ዙሪያ የጎደለውን ለመሙላት፣ የተሻለውን ለማጥበቅ እና ፈጣን ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚረዱ አብራርተዋል።
 
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለይ በሃይል አቅርቦት እና በሎጂስቲክ ዘርፎች የተወሰዱት ማሻሻያዎች ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰት ተጨባጭ ድጋፍ እንደሚሰጡ አንስተዋል።
 
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ በበኩላቸው ሃገሪቱ የጀመረችው ሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የግሉን ዘርፉ ተሳትፎ ለማጎልበት ሰፊ ዕድል እና ተስፋ የሰነቁ ናቸው ብለዋል።
 
በማሻሻያው ላይ በዝርዝር የተመለሱ ጥያቄዎች ለኢንቨስትመንት ፍሰቱ ሳቢ ከመሆናቸው በላይ በተግባር ሂደት ውስጥ ችግር ፈቺ አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
 
የብሪታኒያ – አፍሪካ ኢንቨስትመንት ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በእንግሊዝ ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ መልካም ዕድል የፈጠረ መሆኑን አክለዋል።
 
በመድረኩ ላይ በማዕድን እና የእንፋሎት ሃይል አቅርቦት ዘርፍ አዳዲስ የኢንቨስትመንት ውሳኔዎች ይፋ መደረጋቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.