Fana: At a Speed of Life!

የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በድል ተሻግራ ችግሯን በራሷ ፈታ ወደፊት የቀጠለች መሆኑን የምናሳይበት ነው – መንግስት

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የሚካሄደው 35ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ኢትዮጵያ ፈተናዎቿን በድል ተሻግራ በቁርጥ ቀን ልጆቿ ችግሯን በራሷ ፈታ ወደፊት የቀጠለች መሆኑን የምናሳይበት መሆኑን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ገለፀ።
 
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ ዛሬ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
 
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው፥ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአገራችን እንዳይካሄድ ጠላት ብዙ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፥ የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በመዲናችን እንዲካሄድ መወሰኑ እና በቀጣዩ ሳምንት የሚካሄድ መሆኑ ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለማቀፋዊ ሁነቶችን በሰላም ማስተናገድ የምትችል አገር መሆንዋን ዳግም የሚያሳይ ነው ብለዋል።
 
ጉባኤው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ብዙ ቅስቀሳ እንደነበር አንስተው፥ ሆኖም አባል ሀገራቱ ለህብረቱ ህግና መርህ ተገዢ በመሆን ጉባኤው በአካል በአዲስ አበባ እንዲካሄድ መወሰናቸውን ነው ያመለከቱት።
 
በዚህም ውሳኔያቸው ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት አሳይተዋል ያሉት ዶክተር ለገሰ፥ ይህም ተግባራቸው የሚያስመሰግናቸው ነው ብለዋል።
 
ጉባኤው ኢትዮጵያ ሰላም መሆኑኗን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ የምናሳይበት በመሆኑ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
 
በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የጉባዔው ተሳታፊ አካላት በጎ ትዝታን ጥለው እንዲሄዱ፣ ቤታቸው እና ሀገራቸው ያሉ እስኪመስል ድረስ እንዲሰማቸው እንዲያደርጉ ነው ጥሪ ያስተላለፉት።
 
ደምቀው ያለፉት ሁነቶች
 
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያ ግዙፍና ታላላቅ ክብረ በዓላትን እና ሁነቶችን ሰላማዊ በሆነ መልኩ ማስተናገዷን አንስተዋል።
 
በወይብላ ማርያም ከተከሰተው አሳዛኝ ሁነት ውጭ የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከብሮ ማለፉን እንደዚሁም እስከ 25 ሺህ የሚደርስ ህዝብ የተሳተፈበት ታላቁ ሩጫ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ መካሄዱን ለአብነት አንስተዋል።
 
ከወይብላ ማርያም ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ሁኔታ ግብረ ሀይል ተቋቁሞ እያጣራ መሆኑን ያመለከቱት ሚኒስትሩ፥ የዚህ ውጤት ለህዝብ ይፋ እንደሚደርግ አስታውቀዋል።
 
በአካባቢው እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ለሶስተኛ ጊዜ መሆኑን በመጠቆምም ችግሩን ከስር መሰረቱ ለመፍታት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እየተደረገም ነው ብለዋል።
 
መልሶ ግንባታና የድርቅ ምላሽ
 
በጦርነት ውስጥ የነበሩ አካባቢዎችን የመልሶ ግንባታና አስተዳደራዊ መዋቅሩን የመመለስ ስራም እየተከናወነ መሆኑን ዶክተር ለገሰ ጠቅሰው፥ በዚህም ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
 
ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን ተፈናቃዮች ውስጥ 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ያህሉን ወደ ቀደመ ቀያቸው መመለስ መቻሉን ተናግረዋል።
 
መልሶ በማቋቋም ስራውም በጦርነቱ የታየው የተጋጋለ ስሜት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
 
ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ሆኖም በመንግስት ብቻ ሊቀረፍ አይችልም ሲሉ አስረድተዋል። በመሆኑም በድርቁ የተጎዱ ሰዎችን መድረስ እንዲቻል ለህዝቡና ለዓለማቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች ጥሪ አቅርበዋል።
 
የህወሃት ትንኮሳ
 
በትግራይ ክልል በአየር በሳምንት ሁለት ጊዜ እንዲሁም በየብስ ድጋፍ ለማቅረብ ቢሞክርም አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጥቃት የእርዳታ አቅርቦቱን ማስተጓጎሉን ተናግረዋል።
 
የትንኮሳው ዋና ዓላማው ለትግራይ ህዝብ እርዳታ የሚደርስባቸውን መስመሮች መዝጋት መሆኑን ገልፀዋል።
 
ይህም “ትግራይ ተከባለች” እና “እርዳታ ተከልክለናል” የሚሉ የተምታቱ ፖለቲካዎችን የማራመድ ዓላማ አካል መሆኑን በመጥቀስ፥ ድርጊቱ በትግራይ ህዝብ ላይ ርሀብን ለፖለቲካ መሳሪያነት የመጠቀም ፍላጎቱን ያሳያል ነው ያሉት።
 
በአካባቢዎቹ መከላከያ ሰራዊት መሰማራቱን ያስረዱት ዶክተር ለገሰ፥ አየር ሀይል፣ የአፋር ልዩ ሀይልና ሚሊሻም የሽብር ቡድኑን ጥቃት መመከታቸውን አብራርተዋል።
 
የሚናፈሱ ሀሰተኛ መረጃዎች በህዝብና በመንግስት መካከል መተማመን እንዳይፈጠር የሚፈልጉ ወገኖች የሚነዙት መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
 
መንግስት የሚወስነው የትኛውንም አይነት ውሳኔ የህዝቦች ጥቅም፣ የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት ያስቀደሙ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ ፥ ህዝቡም የመረጠውን መንግስት ሊተማመንበትና የመወሰን ነፃነት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ አሸባሪው ህወሃትና የሽብር ግብረ አበሮቹ የፈጠሯቸው ስጋቶች ለአዋጁ መታወጅ ምክንያት እንደነበሩ አብራርተዋል።
 
ሆኖም የሽብር ቡድኖቹ ስጋትነት በአንፃራዊነት በመርገቡና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በገዳቢነቱ የሚነሳ በመሆኑ፣ በአዋጁ ምክንያት የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስና ያሉ ችግሮችን በመደበኛው ህግ መፍታት ስለሚቻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁ እንዲያጥር ውሳኔ ማስተላለፉንም አክለዋል።
 
 
በአፈወርቅ እያዩና በርናባስ ተስፋዬ
 
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.