Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴው ግድብ የልማት እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም-አብዱልፈታህ አል-ሲሲ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 9፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አል-ሲሲ ለጋራ ሰላምና ብልጽግና ጥሪ አቀረቡ።
ፕሬዚዳንት አል ሲ ሲ ለግብፃውያን፣ ለኢትዮጵያውያን እና ለሱዳኖች ነው ጥሪ ያቀረቡት።
ህጋዊ ድርድር በሰላም አብሮ ለመኖር እና ለመብልጸግ ያስፈልጋል ያሉት አል ሲ ሲ፣ በኢትዮጵያ በኩል ከቀረበው ሀሳብ ጎን መቆም አለብን ብለዋል።
አል ሲ ሲ “የህዳሴው ግድብ የልማት እንጂ ሌላ ጉዳይ የለውም” ማለታቸውን ኢጅብት ቱደይ ጋዜጣ በዘገባው አመላክቷል።
“ለሌሎች መንገር የምንፈልገው ስጋት ቢኖረንም፣ያን ያህል አሳሳቢ አይደለም” ብለዋል አል ሲ ሲ።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያውያንን በልማት ማገዝ እንሻለን፤ “ይህ የሚሆነው ግን የውሃ ድርሻችን የማይነካ ከሆነ ነው” ብለዋል፡፡

አል ሲሲ “በዓለም ዓቀፍ ህግ አግባብ ተስማምተን በሰላም እና ብልጽግና እንኑር” ሲሉም ለኢትዮጵያና ለሱዳን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በንግግራቸው የውሃ ጉዳይና ብሄራዊ ጥቅማቸውን ማስከበር የማይታለፍ ቀይ መስመር መሆኑንም አንስተዋል፡፡

አያይዘውም የግድቡን ወደ ፀጥታው ምክር ቤት የወሰዱት በጉዳዩ ዙሪያ ዓለም ዓቀፉን ማህበረሰብ ትኩረት ለማግኘት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሃገራቸው ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር ብዙ አማራጭ እንዳላት ያነሱት ፕሬዚዳንቱ አማራጮቹንም እንደ አስፈላጊቱ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

“ግብጽ የኢትዮያውያን ብሎም የአፍሪካውያን ህይወት እንዲሻሻል ድጋፍ ማድረግ ትችላለች፤ ይህ ግን የግብጽ የውሃ ድርሻ የማይነካ ከሆነ ብቻ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ይህን ተፈጻሚ ለማድረግ ሰጥቶ የመቀበል መርህን እንደሚከተሉም አንስተዋል፤ ከዚህ አንጻርም ያቀረቡት ጥሪ ጤናማ እንዳልሆነ ማሳያ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.