Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብን በስጦታ ወይም በሌላ ወገን ይሁንታ የምንገነባው አለመሆኑ ሊታወቅ ይገባል-መንግስት

አዲስ አበባ፣ የካቲት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን የምትገነባው ግድብ የመገንባት ሙሉ መብት ስላላት መሆኑን አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለፁ።

የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ አቶ ገዱ እንዳሉትም ኢትዮጵያ የራሷን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅማ ዜጎቿን ከድህነት የማላቀቅ ሙሉ መብት አላት።

ሆኖም አባይን የመሰለ የተፈጥሮ ሀብቷን ስታለማ በዚህ ወንዝ ላይ ህይወታቸውን የመሰረቱ የታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት በመኖራቸው የምትገነባው ግድብ በእነዚህ ሀገራት ላይ ጉልህ ተፅእኖ እንዳያሳድር በማድረግም ነው ብለዋል።

ከግድቡ ዲዛይን ጀምሮ ግንባታውን ይህንን ታሳቢ በማድረግ እያከናወነች ትገኛለችም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ግድቧን ብትገነባም የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ማረጋገጫ የሚፈልጉ እንደመሆናቸው ወደ ድርድር መገባቱን አቶ ገዱ ገልፀዋል።

በዚህ የድርድር ሂደትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተደራድረው ልዩነታቸውን ማጥበብ መቻላቸውን ነው ያነሱት።

በአሜሪካ ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮችም በርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ቢደረስም ከቴክኒክም ሆነ ከህግ አኳያ ገና ያልተግባባንባቸው ጉዳዮች አሉ ብለዋል።

በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በመነጋገር በድርድር እፈታለሁ ብላ ኢትዮጵያ እንደምታምን እና አንዳንዶቹ ጉዳዮች ላይ ጊዜ በመውሰድ በደንብ መነጋገር እንደምትፈልግ ገልፀዋል፤ በድርድሩ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚገባ መሆኑን በመጥቀስ።

በግብፅም ሆነ በአሜሪካውያኑ በኩል ስምምነቱ ቶሎ እንዲፈረም የመፈለግ አዝማሚያ መኖሩን ያመለካቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ ሆኖም የኢትዮጵያ ህዝብ ጉዳዩን በደንብ መገንዘብ መሳተፍ አለበት፤ ይህም ጊዜ ይወስዳል ብለዋል።

ከዚያ ውጭ በድርድሩ ሂደት የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ሚናም ጉዳይ ሌላው ሊፈታ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል፥ እነዚህ ወገኖች ከታዛቢነት አልፎ ህግ አርቅቆ የማቅረብ ፍላጎት አላቸው ነው ያሉት።

ለሁሉም መፍትሄ የሚሆነው መደራደር እና በመጨረሻም ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ መሆኑን ግብፅ ተገንዝባ የምታሰማው ዛቻ ጥቅም የለሽ፣ ለማንም የማይጠቅም እና ግንኙነትን ከማሻከር ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው ልትገነዘብ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በድርድሩ ሂደት ሱዳን ግድቡ ይጠቅመኛል የሚል ጠንካራ አቋም እንዳላት ያነሱት አቶ ገዱ፥ የአባይ ውሃን የመቆጣጠር ፍላጎት ያላት ግብፅ ብቻ መሆኗን አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በድርድር መርህ ላይ ተመስርታ፤ አንዳንዴም ለታችኛዎቹ የተፋሰሱ ሀገራት የበለጠ ተጨንቃ እየሰራች መሆኑን በማንሳት ግድቡንም በዚሁ መሰረት እየገነባች ነው ብለዋል።

አሜሪካ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሀገራቱ በራሳቸው ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ግፊት በማድረግ በጎ ሚናዋን ብቻ እንድትወጣ ኢትዮጵያ እንደምትፈልግ እና ከዚህ ያለፈ ሚና ማንንም እንደማይጠቀም እና በሌላ ተፅዕኖ የሚሆን ነገር እንደሌለ አረጋግጠዋል።

የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው ስለ ግድቡ ወቅታዊ የግንባታ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸው የግድቡ ግንባታ ከብረት ስራ፣ ከተርባይን ተከላ እና ከተቋራጮች አቅም ውስንነት ጋር ተያይዞ ከነበሩበት ችግሮች ወጥቶ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በቅርቡም የግድቡ ግንባታ ሂደትን ለመገምገም ሁሉም ተቋራጮች በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተጠርተው ውይይት እና ግምገማ መደረጉን ገልፀዋል።

በቻይና የተቀሰቀሰው የኮሮና ቫይረስ አስፈላጊ እቃዎች በፍጥነት ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ የተወሰነ እክል መፍጠሩን ያነሱት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፥ በተቻለ ፍጥነት ግን ግንባታውን በማከናወን አሁን ላይ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።

ሀምሌ ወር ላይ ግድቡ ውሃ መያዝ እንደሚጀምር በማረጋገጥም በዚህ ጊዜ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ እንደሚያዝ ግልፅ አድርገዋል።

ያንን ተከትሎም በየካቲት እና መጋቢት ወር አካባቢ ሙከራ እና ሀይል የማመንጨት ስራ ይጀመራል ብለዋል።

 

በህዳሴ ግድብ ላይ እየተካሄደ ካለው ድርድር ጋር ተያይዞ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፥ ከውሃ ሙሌትና አለቃቅ ጋር ተያይዞ ተገቢ ያልሆኑ የህግ ማዕቀፎች እንዲቀርቡ አንፈልግም ሲሉም ተናግረዋል።

ከግድቡ ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በግልፅ የተቀመጠ ነው፤ ከዚያ ውስጥ ድርቅ ሲከሰት የሚለው ነው የሚያከራክረው፤ ይህ እስኪፈታ ጊዜ ይጠይቃል ነው ያሉት ሚኒስቴሩ።

የምንፈርመው ስምምነት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፤ ከህዝብ ጋር፣ ከሚመለከታቸው የዘርፉ ተቋማት ጋር በቂ ውይይት አድርገን ነው መፈረም ያለብን ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፥ ከዚህ በዘለለ ግን ብቁ ያልሆነ ሰነድ ሲቀርብ አንፈርምም ብለዋል።

ከአሜሪካ ሚና ጋር በተያያዘም ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የቴክኒክ ስብሰባ ላይ አደራዳሪም ሆነ አመቻች እንደማትፈልግ በግልፅ አስቀምጣ የነበረ ቢሆንም፥ በአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጥያቄ መሰረት በታዛቢነት እንዲገቡ መደረጉንም ነው ያነሱት።

በአራቱ የቴክኒክ ስብሰባዎች ላይም አሜሪካ በዚሁ ሚናዋ ነበር የቀጠለችውም ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.