Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም ደብዳቤ ለአሜሪካ የግምጃ ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገብረማርያም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በሚያደርጉት ድርድር ውስጥ የዩናይትድ ስቴትስን ሚና በተመለከተ በግላቸው ለሀገሪቱ የግምጃ ቤት ኃላፊ ደብዳቤ ፃፉ።

የአሜሪካ የገምጃ ቤት ሀላፊ ስቴቨን መኑሸን በዋሽንግተን ሲደረግ ነበረው የሶስቱ ሀገራት ድርድር ላይ አሜሪካን ወክለው ሲሳተፉ ነበር።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ በደብዳቤያቸው አሜሪካ በድርድሩ ውስጥ ከአሜሪካ ህግ እና ከፍትሃዊነት መርህዎች አንፃር ሊኖራት ስለሚገባው ሚና የግላቸውን ምክረ ሀሳብ በደብዳቤያቸው አስፍርዋል።

በዚህ ደብዳቤያቸውም ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ከግብፅ ጋር ከዚህ በፊት ስታደርጋቸው የነበረቻቸውን ንግግሮችም ሆኑ ድርድሮች ላይ ሁልጊዜ ሰላምን ስትመርጥ እንደነበር እና በሁለትዮሽ ግንኝነቷም ሁልጊዜ መሻቷ ሰላም እንደነበረ፥ በተቃራኒው ግብፅ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ብቸኛ የበላይ የሆነ ተጠቃሚነትን ለማስጠበቅ በታሪኳ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነትን ስታውጅ እንደኖረች እና አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ለግብፅ ፍላጎቶች የማትገዛ ከሆነ ጦርነት አማራጭ መሆኑን እያስፈራራች መሆኑን ዩናይትድ ስቴትስ ልታውቅ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሚኒስትሩ የሚመሩት የአሜሪካ የገንዘብ መስሪያ ቤት በግድቡ ድርድር ላይ ያለው ተሳትፎንም በተመለከተ የሀገሪቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤትን ሚና የቀማ መሆኑንም በደብዳቤያቸው አመልክተዋል።

አሜሪካ በደርድሩ ውስጥ በሚኖራት ተሳትፎ ውስጥ ሌላው ከግንዛቤ ልታስገባ ይገባል ያሉት ጉዳይ ኢትዮጵያ በእኩልነት እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም መርህ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ወንዟን የመጠቀም መብት እንዳላት ነው ብለዋል።

መስሪያ ቤታቸው በሶስቱ ሀገራት ስምምነት ተደርሶ በፈረንጆቹ የካቲት ወር 2020 ላይ ሊፈረም የነበረውን ሰነድ ይፋ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

እንደዚሁም በዩናይትድ ስቴትስ ድጋፍ ሊቀጥል ከሚችል የትኛውም በግድቡ ዙሪያ የሚደረግ ድርድር ከመጀመሩ በፊት በፈረንጆቹ የካቲት 28 ቀን 2020 ላይ ለፊርማ ቀርቦ የነበረው የስምምነት ሰነድ በይፋ መሻር ይገባዋልም ነው ያሉት።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ያሉትን አለመግባባቶች ለመፍታት የሚደረገው ጥረት ዩናይትድ ስቴትስ እና ሜክሲኮ መሰል ድንበር ተሻጋሪ ወንዝን ለመጠቀም ከደረሱት ስምምነት የተግባር ልምድ ሊቀምር እንደሚገባም አሳስበዋል።

“ኢትዮጵያ የየካቲት 28ቱን ስምምነት የማትፈርም ከሆነ ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ መቀነስ፣ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የምታገኘውን የገንዘብ ብድር ማደናቀፍ እና የሁለትዮሽ የንግድ እና ኢንቨስትመንት እድሎችን ማቀዛቀዝ ይግባል” ብለው አንዳንዶች የሚያቀርቡት ሀሳብ ምንም ጥቅም የማይኖረው፣ ምናልባትም አሁን ያለውን ውጥረት የሚያባብስ እና ሊታሰብ የማይገባው ነው ብለዋል በደብዳቤያቸው።

በመጨረሻም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ የተፈጠረው አለመግባባት በአፍሪካውያን ሀገራት መካከል መሆኑን በማንሳት፥ ዩናይትድ ስቴትስ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ ለሚለው መርህ እውቅና እንድትሰጥ እና ሀገራቱ ችግሩን በራሳቸው የአፍሪካ ህብረትን የመሰሉ ተቋማቶቻቸውን ተጠቅመው እንዲፈቱ እንድታስችል ነው የመከሩት።

በጉዳዩ መግባት አለብኝ ብላ ከወሰነች ግን የአሜሪካ ትረሸሪ ዲፓርተምንት ጉዳዩን ለሚመለከተው ለሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንዲያስረክብ ጠይቀዋል።

ፕሮፌሰር ዓለማየሁ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ትረስት ፈንድ አማካሪ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሲሆኑ፥ በካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.