Fana: At a Speed of Life!

የህግ የበላይነትን በማስከበር የተረጋጋች አገር ለመገንባት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል – የሀረሪ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህግ የበላይነትን በማስከበር የተረጋጋች አገር ለመገንባት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል የሀረሪ ክልል የፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

የሀረሪ ክልል የፀጥታው ምክር ቤት በወቅታዊ ክልላዊ የጸጥታ ጉዳዮች ላይ በመወያየት መግለጫ ሰጥቷል።

የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ከሰሞኑን በምእራብ ወለጋና በጋምቤላ ክልል በሰላማዊ ዜጎች ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ጥቃት በማውገዝ በቀጣይ መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር የተረጋጋች አገር ለመገንባት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጫው አስታውቋል።

ህግ የማስከበሩ ስራ የመንግስት የቀጣይ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አስታውቋል።

የክልሉ የፀጥታ ሀይል ከሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ከብሔራዊ መረጃ እና ደሕንነት፣ ከፌዴራል ፖሊስና ከኦሮሚያ ክልል የፀጥታ ሀይል እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት እየሰራ ይገኛልም ብሏል።

በክልሉ የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ በተለይም ህገ ወጥ ግንባታ እና የመሬት ወረራን ለመከላከል ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን በሀይማኖት ተቋማት ይዞታና በትምህርት ቤቶች የሚካሄዱ የመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታ በክልሉ የፀረ ሰላም ሀይሎች የሀይማኖት ግጭት ለማስነሳት የሚከተሉት ስልት ስለሆነ የፀጥታ አካሉ ከሰላም ፈላጊው ህዝብ ጋር በመቀናጀት የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክቷል።

በተጨማሪም ጽንፈኝነትን መነሻ ያደረገ የሀይማኖት ግጭት ለማስነሳት የሚፈልጉ የፀረ ሰላም ኃይሎች የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም በህዝቦች መካከል ጥርጣሬና ጥላቻን በመንዛት እንዲሁም ህዝባዊ አመጽ በመቀስቀስ ክልሉን እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አካላት ከድርጊታቸው ካልታረሙ ህጋዊ እርምጃ እንደሚሰድ አስገንዝቧል።

ወንጀልን ከመከላከል አንጻር በሀረር ከተማ ተሰማርተው የነበሩ የተለያዩ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲሰጥባቸው ማድረግ ተችሏልም ነው ያለው።

ከትራፊክ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በተወሰደው እርምጃ ሕግ ማስከበር ስራ ለውጦች መመዝገባቸውን ገምግሟል።

በህገ ወጥ የሰው ዝውውር ከመከላከል፣ አደገኛ እፅ ከመቆጣጠር አንፃር ፣ ኮንትሮባንድን እና ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል ረገድ እና ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ከመቆጣጠር አንፃር በተሰራው ዘመቻ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አስታውቋል።

ለዚህ ስራ ውጤታማነትም ግብረሃይል ተቋቁሞ በየጊዜው በክልሉ የፀጥታው ምክር ቤት እየተገመገመ መልካም ተግባራት እንዲጎለብቱ እና በሂደቱ የታዩ ክፍተቶችም በአፋጣኝ እንዲታረሙ እየተደረገ ነው ብሏል ምክር ቤቱ።

የህግ የበላይነትን በማስከበር በተከናወኑ ተግባራት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሲያደርግ የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምክር ቤቱ ጥሪውን አቅርቧል።

በመሆኑም ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብ ከፀጥታ ሀይሉ ጋር በመቀናጀት እና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ ዛሬም እንደ ትናንቱ የክልላችን ህዝቦች በሰላም፣ በአብሮነት እና በመቻቻል የሚኖሩባት ክልል መሆኗን በተግባር እንደሚያረጋግጥ ይተማመናል።

ከዚህ በተጨማሪ በሀይማኖት አክራሪነትና ጽንፈኝነት፣ በማህበራዊ ሚዲያ፣ በማህበረሰብ አንቂነት፣ በፖለቲካ ቡድን እና በብሔር ስም የሚደረግ ሀገር የማፍረስ ሤራን የጸጥታ ምክር ቤቱ በምንም መልኩ እንደማይታገሥ አስገንዝቧል።

የክልሉን ሰላምና ጸጥታን የማስፈን እና ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብሏል በመግለጫው።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.