Fana: At a Speed of Life!

የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 23፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል በሰላም መከበሩን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ኮሚሽኑ በመግለጫው ለበዓሉ በሰላም መከበር ድጋፍ ላበረከቱ አካላት ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

አባገዳዎች፣ አደ ስንቄዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የተከበረው የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም መከበሩን ነው ያስታወቀው፡፡

ለበዓሉ በሰላም እንዲከበር የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ዕቅድ በማውጣት እና ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎቹን በማወያየት ወደ ስራ መግባቱን፥ አስታውሶ ልዩ ልዩ አካላትን ያሳተፈ የፀጥታ ስራ በመሰራቱ በዓሉን በሰላም ማክበር እንደተቻለ ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ለበዓሉ ስኬታማነት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት እና የበዓሉ ታዳሚዎች ላደረጉት ቀና ትብብር፤ ደከመን ሰለቸኝ ሳይሉ ህዝብና መንግስት የጣሉባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለተውጡ ለከተማው አስተዳደር፣ ለሀገር መከላከያ፣ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ፣ ለሪፐብሊካን ዘብ ፣ ለፌዴራል፣ ለኦሮሚያና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮችና አባላት በፀጥታ ግብረ ኃይሉ ስም ኮሚሽኑ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በተለይም መላው የከተማችን ነዋሪዎች ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ በዓሉ በሰላም እንዲከበር ለማስቻል መረጃዎችን ለፀጥታ ኃይሉ በማቀበል የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይከሰት በፖሊስ የተላለፉ መረጃዎች በመቀበልና ለትራፊክ ፖሊስ አባላት ተባባሪ በመሆን ህብረተሰቡ ለነበረው የተለመደ ቀና ትብብር የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምስጋናውን በማቅረብ በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.