Fana: At a Speed of Life!

የሐረሪ ክልል መንግስት የኮሮና ቫይረስ ስጭትን ለመከላከል የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ ፣መጋቢት 17፣2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐረሪ ህዝብ ክልላዊ መንግስት የመስተዳድር ምክር ቤት የኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፥ ሁሉም የመንግስት ተቋማት ለአካል ጉዳተኛ፣ ዕድሜያቸው 50 ዓመትና በላይ ለሆኑ፣ ለነፍሰ ጡርና አጥቢ እናቶች፣ ከቫይረሱ ጋር ተዳብለው ጉዳት የሚያስከትል ህመም ላለባቸው ሰራተኞች እንዲሁም በየመኖሪያቸው ገጠር ሆኖ ከተማ ባለ የመንግስት ተቋም ለሚሰሩ ሰራተኞች ፍቃድ በመስጠት ቤታቸው እንዲቆዩ ማድረግ እንዳለባቸው አስታውቋል።

በክልሉ ማንኛውንም አይነት ስብሰባዎችን ማካሄድ በጥብቅ የተከለከለ መሆኑን የገለጸው ምክር ቤቱ፥ አስቸኳይ እና የማይቀየሩ ስብሰባዎች ሲያጋጥሙ የተሰብሳቢዎችን ቁጥር ከ15 ያልበለጠ ሆኖ ተሳታፊዎች በየአንድ ሜትር ርቀት እንዲቀመጡ አሳስቧል።

ከዚህ ባለፈም ህዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው እና የሚጠቀምባቸው መጠጥ ቤቶች፣ የምሸት ጭፈራ ቤቶች እና ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን ከፍቶ አገልግሎቱን መስጠት የተከለከለ መሆኑን ከክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በሁሉም መንግስትና የግል የጤና ተቋማት ተኝተው ለሚታከሙ ህሙማን ከአንድ በላይ አስታማሚ ማስገባት፣ የስፖርት ውድድሮች፣ የአካል ብቃት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ መዋኛ ቦታዎች እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ የመዝናኛ እና የመጫወቻ ስፍራዎችን ከፍቶ አገልግሎት መስጠትም ሆነ መጠቀም መከልከሉ ተገልጿል።

በተለያዩ የእምነት ተግባራት ማከናወኛ ስፍራዎች በተለመደው መልኩ በጋራ በመሰብሰብና በመጠጋጋት የአምልኮ ስነ ስርዓት ማከናወን በከፍተኛ ደረጃ ለቫይረሱ መያዝና መሰራጨት ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ ያስቀመጡትን አቅጣጫዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም ተመላክቷል።

በሀገር እና በህዝብ ላይ የተደቀነ ግልጽ አደጋን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም በማንኛውም የፋብሪካ እና የግብርና ምርቶች የዋጋ ጭማሪ ማድረግም ሆነ መደበቅ የህዝባችንን በችግር ጊዜ የመረዳዳት እሴት የሚፃረርና አስነዋሪ ተግባር ከመሆኑ በተጨማሪ በህግ የሚያስቀጣ የወንጀል ድርጊት መሆኑንም አስገንዝቧል።

ከተለያዩ የአለም ሀገራት ወደ ክልሉ ለጉብኝት ወይም ለሌላ ጉዳይ በሚመጡ የውጭ ዜጎች ላይ ማናቸውም አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጉዳት መፈፀም በጥብቅ የተከለከለና የሚያስጠይቅ የወንጀል ተግባር መሆኑን መገንዘብ እና መቆጠብ እንደሚገባ አሳስቧል።

በክልል ደረጃ የኮረና ቫይረስን ለመከላከልና ህዝባችንን ለመታደግ በሚደረገው ርብርብ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ አካላትና ግለሰቦች በክልል ደረጃ በሚቋቋመው የሀብት አፈላላጊ ኮሚቴ በኩል ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.