Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን ሲያሰራጩት የነበረውን ሀሰተኛ መረጃ ያጋለጠ ነው – ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 17 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን ሙሌቱ ጉዳት ያደርስብናል በማለት ሲያሰራጩ የነበረውን የሀሰት መረጃ እንዳጋለጠ የዓረብ ሃገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ ገለጹ።

የግድቡ ውሃ ሙሌት በታችኛው ተፋሰስ ሃገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ማሳያም ነው ብለዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መገባደዱን በተያዘው ሳምንት መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያና የዓረብ ሃገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን በሙሌቱ ምክንያት የውሃ እጥረት ያጋጥመናል ብለው ሲያሰራጩት የነበረውን የሀሰት መረጃ ያጋለጠ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሙሌቱ ሁለቱ ሃገራት የግድቡን ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ እንዳይሞላ ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት ፍሬ አልባ ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

የውሃ ሙሌቱ የተከናወነው በፈረንጆቹ 2015 ሶስቱ ሃገራት በሱዳን ካርቱም በፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት አማካኝነት ነው ብለዋል።

“ኢትዮጵያ ሙሌቱን ያደረገችው በጥንቃቄና የታችኞቹ ተፋሰስ ሃገራት ላሉባቸው ስጋቶች ምላሽ በሰጠ መልኩ ነው፤ ዓለም ሙሌቱ የተሳካ እንደነበር ለማየት ችሏል” ሲሉ ነው አል-ሀሪሪ የገለጹት።

እስካሁን የተከናወኑ የግድቡ ስራዎች ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ማንም ላይ ጉልህ ጉዳት ለማድረስ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት እንዲረዱት ያስችላቸዋል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በተጨማሪ ሁለት የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ተርባይኖች ማንቀሳቀስ የሚያስችል የውሃ መጠን መያዝ መቻሉን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸው ነበር።

ሁለቱ ተርባይኖች በወራት ጊዜ ውስጥ ሃይል እንደሚያመነጩ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

ተርባይኖቹ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ስራ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ትልቅ የሚባል ስኬት እንደሆነ ነው ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ የሚገልጹት።

በተጨማሪም ሙሌቱና የተርባይኖቹ ስራ መጀመር ሕዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግብጽና ለሱዳን እንዲሁም ለቀጠናው ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነም አመላክተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን የአቋም ለውጥ አሳይተው ወደ ድርድር እንዲመጡ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ነው አል-ሀሪሪ ግምታቸውን ያስቀመጡት።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.