Fana: At a Speed of Life!

የሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል አለበት – ኢንጂነር ስለሺ በቀለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደለል እንዳይሞላ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ አሳሰቡ።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትና የተጠሪ ተቋማት ሠራተኞች በሱሉልታ ወረዳ ደርባ ከተማ አካባቢ የአረንጓደ አሻራቸውን አሳርፈዋል።

የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማቱ ሠራተኞች በዚሁ ሥፍራ ከ27 ሺህ 700 በላይ ችግኖችን ተክለዋል።

በችግኝ ተካላው ወቅትም “ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራን ከራሷ አልፎ ለተፋሰሱ ሀገራትም ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው” ተብሏል።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ችግኞችን መትከል አካባቢን ከመራቆት ከመከላከል ባሻገር ለትላልቅ ፕሮጀክቶች ዘለቄታዊ ዋስትና መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራን በዋናነት ለራሷ ነው የምትሰራው ያሉት ሚኒስትሩ የተፋሰሱ ሀገራት ውኃ እንዲያገኙ ያስችላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ሥራ የአፈር መሸርሸርን ስለሚያስቀር የተፋሰሱ ሀገራት ፕሮጀክቶችም በደለል እንዳይሞሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አውስተዋል።

የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር አብረሃ አዱኛ በበኩላቸው የሕዳሴ ግድቡ የሁሉም አሻራ ያረፈበት በመሆኑ ከወዲሁ ልንከባከበው ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በበኩላቸው እየተለወጠ የመጣውን የአየር ጠባይ ለማስተካከል ችግኝ መትከል አስፈላጊ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.