Fana: At a Speed of Life!

የመሰረተ ልማት ተቋማትን ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመሰረተ ልማት ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች እና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በጅማ ከተማ ተካሄደ።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፋንታ ደጀን፥ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑና የዘርፉ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልኩ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ለማስቻል ስራው በሚኒስቴሩ እንዲመራ መደረጉን ጠቁመዋል።

የመሰረተ ልማት ዘርፍ ከአስፈፃሚ ተቋማት የተቀናጀ የጋራ ዕቅድ በማዘጋጀትና አፈፃፀሙን በመገምገም በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በሚኒስቴሩ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅትና አፈፃፀም ድጋፍ ዳይሬክተር አቶ እስማኤል አብደላ፥ የመድረኩ ዓላማ የመሰረተ ልማት ሀገራዊ የተቀናጀ ልማት ትግበራ ላይ በቅንጅት እጦት ምክንያት የሚፈጠረውን የጊዜና የሀብት ብክነት ለመቀነስ እንዲሁም የመንግስትንና የህብረተሰቡን የመሰረተ ልማት ፍላጎት ለማሟላት በጋራ ለመስራት እንዲቻል የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሠረተ ልማት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ፣ ኢትዮ-ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፣የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ሪፖርት ቀርቦ በጋራ አፈፃፀም ወቅት የታዩ ጠንካራ ጎኖችና ክፍተቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

በመድረኩም ከመሰረተ ልማት ይዞታዎች ከሚነሱ የካሳ አተማመንና አፈፃፀም ጋር በተያያዘ በወቅቱ የካሳ ክፍያ አለመክፈል ፣ የበጀት እጥረትና የወሰን ማስከበር፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እና በጀት አለመጠናቀቅ በውይይት መድረኩ ላይ ተነስተው በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።

በመድረኩ ላይ ከጋምቤላ ክልል መስተዳደር፣ ምዕራብ ኦሮሚያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የተውጣጡ ሁሉም ዞኖች፣ ከተማ አስተዳደሮች ፣ የመሰረተ ልማት ተቋማት የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.