Fana: At a Speed of Life!

የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የሚስተዋለውን የአዋጭነት ጥናትና የዲዛይን ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል አውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር በመስኖ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝ የምክክር አውደ ጥናት በቢሾፍቱ ከተማ እያካሄደ ነው።

አውደ ጥናቱን በንግግር የከፈቱት የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ዴኤታ ተወካይ ኢንጂነር ሳሙኤል ሁሴን፥ መንግሥት ለመስኖ ልማት ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

18 ቢሊየን ብር በመመደብ የትላልቅና የአነስተኛ ግድቦች ግንባታ እየተከናወነ መሆኑን ጠቅሰው፥ ዘርፉ አሁንም ችግሮች እንዳሉበት፣ በአነስተኛና ትላልቅ የመስኖ ፕሮጀክቶች ላይ የአዋጭነት ጥናት፣ የዲዛይንና የግንባታ መጓተት ፈተና መሆናቸውን ዘርዝረዋል።

በዚህም ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ለማጠናቀቅ አለመቻሉን በማንሳት የፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናቸው ከፍተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት።

የምክክር አውደጥናቱ ዋና ዓላማም ፥ በፕሮጀክቶች ላይ የሚታዩ የአዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

ፕሮጀክቶቹ የሚገነቡበት አካባቢን የሥነ-ምህዳር፣ የውሃና የአፈር እንዲሁም የአየር ሁኔታን ለማጥናትና የጂኦስፓሻል መረጃዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋል የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መሆኑም ተገልጿል፡፡

በአውደ ጥናቱ የስፔስ ሳይንስ፣ የጂኦስፓሻልና የሚቲዮሮሎጂ ቴክኖሎጂዎችና መረጃዎች ለመስኖ ፕሮጀክቶች አዋጭነት ጥናትና ዲዛይን ያላቸው ፋይዳ ላይ ያተኮሩ የመወያያ ፅሁፎች ቀርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.