Fana: At a Speed of Life!

የመንግስት ስራዎችን በዲጂታል መልክ የሚያሰሩ ማዕከላት በ6 ተቋማት ሊቋቋሙ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመንግስት ስራዎችን በዲጂታል መልክ ለመስራት የሚያስችሉ የስራ ትስስር ማዕከላት በ6 ተቋማት ሊቋቋሙ ነው፡፡
የስራ ትስስር ማዕከላቱ የመንግስት ስራዎች በግንኙነቶች ሳይቆራረጡ፣ ጊዜና ቦታ ሳያግዳቸው በዲጂታል መልኩ እንዲሰሩ የሚያደርግ አሰራር የሚተገበርባቸው መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በመጀመሪያው ምዕራፍ በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለስልጣን እና በብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ናቸው ተብሏል፡፡
ፕሮጀክቱን በጨረታ ያሸነፈው አይ ኢ ኔትወርክ ሶሉሽን የሚሰራው ሲሆን÷ በ120 ቀናት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ስምምነት ፈርሟል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ÷ የዲጂታል 2025 ስትራቴጂ ያለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እውን ስለማይሆን በሁሉም የልማት ስራዎች የግል ዘርፉ አጋር ብቻ ሳይሆን ባለቤትም እንዲሆን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
በዲጂታል ፋውንዴሽን ፕሮጀክት ስር በመተግበር ላይ ካሉት ስራዎች ውስጥ የመንግስት የስራ ትስስር ማዕከል ልማት አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ስርዓቱ የመንግስት ተቋማት ስራዎች ጊዜና ቦታ ሳይገድባቸው የሚከወኑበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ ትግበራ በ50 የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ክልሎች ጭምር ተግባራዊ ይደረጋል መባሉን ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.