Fana: At a Speed of Life!

የመከላከያ ሰራዊት የመጨረሻውንና ሶስተኛውን የዘመቻ ምዕራፍ እንዲፈፅም ትዕዛዝ መሰጠቱን ጠ/ሚ ዐቢይ አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 17፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመከላከያ ሰራዊት የመጨረሻውንና ሶስተኛውን የዘመቻ ምዕራፍ እንዲፈፅም ትዕዛዝ እንደተሰጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
“በዚህ ዘመቻ ለንፁሃን ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን፤ በህዝባችን ላብ የተሰራችው የመቐለ ከተማ የከፋ ጉዳት እንዳያገኛት የሚቻለውን ሁሉ ይደረጋል” ብለዋል ባወጡት መግለጫ።
የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
የመጨረሻው የዘመቻው ምእራፍ ተጀምሯል።
የተሰጠው የ72 ሰዓት ጊዜ ተጠናቋል፤ ህግ የማስከበር ዘመቻው የመጨረሸው ምእራፍ ላይ ደርሷል። በተሰጠው የ72 ሰዓት ጊዜ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ አባላት እጃቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ሰጥተዋል።
ብዙ የትግራይ ወጣቶችም የህወሓትን እኩይ አላማ ተረድተው እጃቸውን ሰብስበዋል። ይህ በመጨረሻው ሰዓትም ቢሆን የተወሰደ ሀላፊነት የሚሰወማው ውሳኔ ህሊና ካለው ፍጡር የሚጠበቅ ውሳኔ ነው።
መንግስት 72 ሰዓት ሲሰጥ አላማው ሁለት ነበር። በአንድ በኩል ዋና ፍላጎቱ ህግ ማስከበር እንጅ ጦርነት አለመሆኑን መግለጥ ነው።
ወንጀለኛው ጁንታ በሰላም እጁን ለመስጠት ከቻለ ዘመቻውን በማጠናቀቅ ህግን በአነስተኛ ዋጋ ለማስከበር ይቻላል ብሎ ያምናል።
ለዚህም ሲባል ተደጋጋሚ እድሎችን ሰጥቶ ነበር። ሁለተኛው ደግሞ የህወሓት የጥፋት አላማ ዘግይቶም ቢሆን የገባው አንድም ሰው ከተገኘ ያንን ሰው ለማትረፍ እንዲቻል ነው።
ለህወሓት ጁንታ የተከፈተው የመጨረሻ ሰላማዊ በር በጁንታው እብሪት ምክንያት ተዘግቷል። የጥፋታቸውን አላማ ተገንዝቦ ለሚመለስ ሰው በተከፈተው በር ግን፤ በሺህዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ሚሊሻ እና ልዩ ሀይል አባላት እጃቸውን እየሰጡ ገብተውበታል።
የመከላከያ ሰራዊታችን የመጨረሻውን እና ሶስተኛውን የዘመቻ ምዕራፍ እንዲፈፅም ትዕዛዝ ተሰጥቶታል። በዚህ ዘመቻ ለንፁሃን ሰዎች ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን፤ በህዝባችን ላብ የተሰራችው የመቐለ ከተማ የከፋ ጉዳት እንዳያገኛት የሚቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
ቅርሶች፣ ቤተ እምነቶች፣ የህዝብ መገልገያዎች፣ የልማት ተቋማት እና የህዝብ መኖሪያዎች የጥቃት ኢላማ እንዳይሆኑ ሁሉም አይነት ጥንቃቄ ይደረጋል።
የመቐለና የአካባቢው ህዝባችን ትጥቁን ፈትቶ በቤቱ በመቀመጥና ከወታደራዊ ዒላማዎች በመራቅ፤ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ሁሉ እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን።
በጥቂት የህወሓት ጁንታ አባላት ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ህዝቡ የጁንታውን አባላት አሳልፎ በመስጠት የበኩሉን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ጥሪ እናደርጋለን።
የመከላከያ ሰራዊታችን በሰላማዊ ዜጎች፣ በቅርሶች፣ በቤተ እምነቶች፣ በልማት ተቋማትና በንብረቶች ላይ ጉዳት ሳይደርስ ጁንታውን ለህግ የሚያቀርብበትን ጥንቃቄ የተሞላው የዘመቻ ስልት የነደፈ መሆኑን ልናረጋግጥላችሁ እንወዳለን።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.