Fana: At a Speed of Life!

የመደጋገፍ እሴትን በማጎልበት አንድነታችንን እናጠናክራለን – የሃይማኖት አባቶች

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመደጋገፍ እና የአብሮነት እሴትን በማጎልበት አንድነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በሀረሪ ክልል የሃይማኖት አባቶች ገለጹ።

በክልሉ በኢድ አልፈጥር በዓል የስግደት ሥነ -ሥርዓት የሚካሄድበትን ቦታ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አጽድተዋል።

በጽዳቱ የተሳተፉ የሃይማኖት አባቶች እንደገለጹት÷የክልሉ እሴት የሆነውን የመደጋገፍ እና የአብሮነት እሴትን በማጎልበት አንድነታቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የተናገሩት።

በክርስትና እምነት በሚከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ የማክበሪያ ቦታዎችን በማጽዳት ፍቅሩንና መደጋገፉን በተግባር እያሳየ መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡

የክርስትና እምነት ተከታዮችም በኢድ አልፈጥርና ኢድ አልአደሃ በዓል ላይ በመገኘት የስግደት ቦታዎችን እንደሚያጸዱ ተናግረዋል።

በሐረሪ ክልል ሙስሊምና ክርስቲያኑ ማዕድ መጋራት እና በዓላቶችን በጋራ ማክበር ለረጅም ዘመናት የነበራቸው የአብሮነት እሴቶት መሆኑም ተገልጿል።

የመደጋገፍ እሴትን በማጎልበት አንድነታቸው ተጠናክሮ እንደቆየ የጠቀሱት የሃይማኖት አባቶች÷ ይህንን በተግባር ለማሳየት የኢድ አልፈጥር የስግደት ሥነ -ሥርዓት የሚከበርበትን ቦታ ዛሬ ማጽዳታቸውን ተናግረዋል።

የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓል ሲከበርም የሀይማኖት አባቶች በጋራ የጽዳት ዘመቻ እንዳከናወኑ ጠቅሰው÷ በቀጣይ የኢድ አልፈጥር በዓል በደማቅ እንዲከበር በጋራ አጽድተናል ብለዋል፡፡

ጽዳት ሲከናወን ውስጥንም በማጽዳት የክልሉ እሴት የሆነውን የአብሮነትና የመደጋገፍ ባህል ማሳደግ እንደሚገባ መገለጹን ከሃረሪ ክልል ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.