Fana: At a Speed of Life!

“የመዲናዋ ህንፃዎች ግራጫ ቀለም ሊቀቡ ነው” በሚል የሚናፈሰው መረጃ ሀሰት መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ህንፃዎች ሁሉ ግራጫ ቀለም ሊቀቡ ነው በሚል ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች የሚናፈሰው መረጃ ከዕውነት የራቀ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዮናስ ዘውዴ አስታወቁ።

የቢሮ ኃላፊው  አዲስ አበባን እንደ ስሟ ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የህንፃ ስታንዳርድና የውጭ ማስታወቂያ ስታንዳርድ እየተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡

ሆኖም ግን ይህን መነሻ አድርጎ በማህበራዊ ትስስር ገጾች አዲስ አበባ ግራጫ ቀለም ልትቀባ ነው በሚል በስፋት ሲዘዋወር የታየው መረጃ የተሳሳተ  መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

እስካሁን ድረስ የከተማዋ ህንጻዎች ቀለም ምን አይነት ይሁን የሚለው ጉዳይ ለውይይት ቀረበ እንጂ የከተማ አስተዳደሩ በጉዳዩ ላይ ምንም አይነት ውሳኔ እንዳላሳለፈ አመልክተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይም ከዚህ ቀደም ‹‹ከተማችን ቡራቡሬ ሆና ባለቤት አልባ መስላለች›› ማለታቸውን ያስታወሱት የቢሮ ኃላፊው፤ ይህን ችግር ማንኛውም የመዲናዋ ነዋሪም ሊታዘብ ይችላል ፤የከተማ አስተዳደሩም ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

ችግሩን ለመፍታት የውጭ ማስታወቂያውና የከተ ማዋ ቀለም ሁኔታ የሚመራበት ስታንዳርድ ዝግጅት ተደረገ እንጂ ውሳኔ ላይ አለመድረሱን ጠቁመዋል።

በቅርቡ በጉዳዩ ላይ ከባለሀብቶች ጋር ውይይት ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው፤ ይህን መነሻ አድርገው አንዳንድ ግለሰቦች ለግራጫ ቀለም የመሰላ ቸውን ትርጓሜ ሲሰጡ ተመልክተናል፡፡ ጉዳዩ በማህበራዊ ትስስር ገጾች እንደሚዘዋወረው ተግባር ላይ የዋለ ሳይሆን ገና ለምክክር የቀረበ መሆኑን መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

ከተማዋ ላይ አንድ አይነት ቀለም ብቻ ለቀለም ቅብ ሥራ ያስፈልጋል የሚል እሳቤ መያዝ እንደሌለበት የተናገሩት ኃላፊ፤ ለአስፈላጊው ህንጻና አካባቢ የሚመጥን ዝብርቅርቅ ያልሆነና ለዓይን የሚማርኩ ቀለማትን የያዘ ስታንዳርድ እንደሚኖረን ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ በተከታታይ በምናደርጋቸው ውይይቶችና የሕዝብ ተሳትፎ መድረኮች ላይ የሚገኙ ግብዓቶችን ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚደረግ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪ ማወቅ አለበት ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የከተማዋ ቀለም ስታንዳርዱን የጠበቀ መሆን አለበት የሚለው ሀሳብ ሁላችንንም ሊያስማማ የሚችል ጉዳይ ነው ያሉት ዮናስ ዘውዴ፤ የከተማው ነዋሪ ያልመከረበትና ስምምነት ላይ ያልደረሰበት ምንም ነገር ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።

በቀጣይነት በሂደቱ ላይ በርካታ ባለድርሻ አካላት እንደሚሳተፉና ተወያይቶ መግባባት ላይ መድረስን እንደሚጠይቅ የጠቆሙት ቢሮ ኃላፊው፤ ሥራው ካለው ስፋት አንጻር ስታንዳርዱ በዚህ ጊዜ ተጠናቆ ወደ ትግበራ ይገባል የሚለውን ለመግለጽ እንደሚቸገሩ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.