Fana: At a Speed of Life!

የመዲናዋ አስተዳደር የቀዳማይ ልጅነት እድገትና እንክብካቤ ፕሮግራምን ልተገብር ነው አለ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከ330 ሺህ በላይ ሕፃናት ድጋፍና እንክብካቤ የሚያገኙበት የቀዳማይ ልጅነት እድገትና እንክብካቤ ፕሮግራም በተሟላ ሁኔታ ወደ ተግባር ሊያስገባ መሆኑ ተገለጸ፡፡
ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ በሁሉ አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት እድገትና እንክብካቤ ፕሮግራም ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ የቢግ ዊን ፊላንትሮፒ ኃላፊ ዶክተር ከሰተ ብርሃን አድማሱ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፥ በመዲናዋ ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሕፃናት የአእምሮ እድገት መጠን ችግሮች ተጋላጭ መናቸውን ገልጸዋል፡፡
ተገቢውን ትኩረትና እንክብካቤ ማግኘት አለመቻላቸውንና ባለመቻላቸው ምክንያት የወደፊት ሕይወታቸው ላይ ተፅእኖ እንደሚያመጣም በአፅንኦት ተናግረዋል።
አክለውም ይህ ሁሉ አቀፍ የቀዳማይ ልጅነት እድገትና እንክብካቤ ፕሮግራም ትውልድ የሚቀይር ፕሮግራም ነው ብለዋል፡፡
ይህ በአፍሪካ መጀመሪያው እንደሆነ የተነገረለት ፕሮግራም፥ በአዲስ አበባ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በ9 ፓኬጆች ከ330 ሺህ በላይ ሕፃናትን ለመድረስ መታቀዱም ተነግሯል፡፡
ከነዚህም ውስጥ ቤት-ለቤት የሚሰጥ የወላጆች ምክርና ድጋፍ፣ በየመንደሩ የሚከፈት አረንጓዴ የሕፃናት መጫወቻ ቦታዎች፣ የሕፃናት ማቆያ ቦታዎች፣የሕፃናት አልሚ ምግብ አቅርቦት እና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡
በመድረኩ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር ÷ ሕፃናት ትልቅ ትኩረት የሚፈልጉ መናቸውን ገልጸው፥ “ሕፃናት ላይ ኢንቨስት ካልተደረገ ሀገር ናትውልድ ችግር ውስጥ እንደሚገባም ሊታወቅ ይገባል” ብለዋል፡፡
ፕሮግራሙ ዓላማ ከሦስት ዓመታት በኋላ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦችና ሕፃናትን በሙሉ የዚህ ፓኬጅ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሆነም ጠቁመዋል ፡፡
በሚቀጥሉት ጊዜያትም አስተዳደሩ በከተማዋ ቤት- ለቤት ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉ አምስት ሺህ ባለሙያዎችን እንደሚቀጥርም ነው ያስታወቁት፡፡
ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ በበኩላቸው÷ ይህ ስራ እንዲሳካ ዋናው የአመራሩ ቁርጠኝነት ነው ማለታቸውን ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.