Fana: At a Speed of Life!

የመድሃኒትና ህክምና ቁሳቁስ እጥረት ህሙማንን ለመርዳት ፈታኝ ሁኔታ ፈጥሯል – የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የመድሃኒትና ህክምና ቁሳቁስ እጥረት ህሙማንን ለመርዳት ፈታኝ ሁኔታ መፍጠሩን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

የተለያዩ የጥቁር አንበሳ ህክምና ባለሙያዎች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ባደረጉት ቆይታ፥ ከግብዓት አቅርቦት ችግሩ በተጨማሪ የክፍያ መዘግየትና የአስተዳደር ችግሮችም ጫና እንደፈጠሩባቸው ተናግረዋል፡፡

የሆስፒታሉ ባለሙያዎች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የህክምና ግብዓት ችግሮች ለስራቸው እንቅፋት እየሆኑ መምጣታቸውን ጠቅሰው፥ ይህም ሙያዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡና ሥነ ልቦናዊ ጫና እንዲደርስባቸው ማድረጉን ያነሳሉ።

እንደባለሙያዎቹ አክለውም፥ መፍትሄ ፍለጋ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው የሚመጡ ህሙማን ለእንግልት ከመዳረጋቸውም በላይ እስከሞት የደረሰ ችግር እያስከተለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢው ያነጋገራቸው የሆስፒታሉ ተገልጋዮችም ችግሩ ከተባለው በላይ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

የሆስፒታሉ አመራር በበኩሉ ፥ በተለያዩ የህክምና ግብዓት ችግር ዋነኛው ምክንያት የበጀት እጥረት መሆኑን ገልጿል።

በጀት የሚመደብለት “የማስተማሪያ ሆስፒታል” በሚል መሆኑን የሚያነሱት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዶክተር አንዱዓለም ደነቀ ፥ ሁኔታዎችን በማቻቻል አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡

ዶክተር አንዱዓለም በበኩላቸው፥ ኤም አር አይን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ መሳሪዎች ብልሽት እንደሚገጥማቸው ፤ ጥገናቸው በከፍተኛ ወጪና በውጭ አገር ዜጎች የሚካሄድ መሆኑ ሁኔታውን እንዳከበደው ነው የሚናገሩት፡፡

“ሆስፒታሉ በዱቤ የመድሃኒት ግዢ 70 ሚሊየን ብር የሚደርስ እዳ እንዳለበት” የሚሉት ዶክተር አንዱዓለም ፥ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ ከድጋፍ፣ ከአጋር አካላትና ከተለያዩ አማራጮች በሚገኝ ምንጭ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ማቴዎስ ኢንሰርሙ ፥ አንዳንድ እጥረቶች ሆስፒታሉ ካለው አቅም በላይ ህይወት ለማሰንበት በመስራቱ የተፈጠሩ መሆናቸውንና የበጀት እጥረት እንዳለበት ገልጸው፣ የመፍትሄ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ከቀጣዩ ዓመት ጀምሮ ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡

ቅሬታቸውን ለፋና ያቀረቡ የሆስፒታሉ ባለሙያዎች በተጨማሪ የሚያነሱት ፥ በ2012 ዓ.ም ተፈፃሚ መሆን የነበረበት የኮቪድ-19 ክፍያ ዛሬም ድረስ ሙሉ ለሙሉ እንዳልተፈፀመላቸው ነው፡፡

ቅሬታቸውን ለሚመለከተው ማሰማታቸውን ያነሱት ባለሙያዎቹ ፥ በከፈል ካለበት ክፍያ ውስጥ 34 በመቶ ያህሉ አሁንም እንዳልተከፈላቸውና ለእንግልት መዳረጋቸውንም ያነሳሉ፡፡

የሆስፒታሉ ሰራተኞች ሌላው የሚያነሱት ቅሬታ ፥ የተረኝነት ክፍያን (ዱቲ) የሚመለከት ሲሆን ፥ ቅሬታ የተነሳበት የሥራ ሂደትም የክፍያ ሁኔታው እንደሚዘገይና ይህም የተለመደ እንደሆነ ነው የሚያነሳው፡፡

አሁን ቅሬታ የተነሳበትን ክፍያ ለመፍታት መግባባት ላይ መደረሱንና ከነገ ጀምሮ ክፍያው ተግባራዊ እንደሚደረግ ዶክተር አንዱዓለም ደነቀ ይናገራሉ፡፡

የኮቪድ-19 ክፍያን በተመለከተ በጊዜው መረጃ እንዳልደረሰውና ለመፍትሄው መረጃ የማጣራት ስራ እየተሰራ መሆኑን፣ ጉዳዩ ከተጣራ በኋላ ከሚመለከተው ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር እንደሚከፍል ነው ዩኒቨርስቲው የገለጸው፡

በአፈወርቅ እያዩ

ኢትዮጵያን፦ እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ!

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.