Fana: At a Speed of Life!

የመገናኛ ብዙሃንና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነምግባርና አሰራር ረቂቅ መመሪያ ውይይት እየተደረገበት ነው

አዲስ አበባ ፣ ጥር 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለምርጫው ማስፈፀሚያ ባዘጋጃቸው መመሪያዎች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፡፡

የመገናኛ ብዙሃን እና የጋዜጠኞች የምርጫ አዘጋገብ የስነምግባር እና አሰራር ረቂቅ መመሪያ እና የስነዜጋ እና የመራጮች ትምህርት ፈቃድ አሰጣጥ እና ስነምግባር ረቂቅ መመሪያ ናቸው ውይይት የተካሄደባቸው።

መገናኛ ብዙሃኑን የተመለከተው መመሪያ የመገናኛ ብዙሃን ከምርጫ በፊት ፣ ምርጫው በሚካሄድበት ወቅት እና ከምርጫ በኋላ አዘጋገባቸው ሂደቱን የማያውክ፣ ሚዛናዊና እውነተኛ ምንጭን ማዕከል ያደረገ እንዲሁም ለምርጫው ገለልተኝነት የራሱን ሚና እንዲጫወት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

መመሪያው ፈቃድ አሰጣጥን እና ፈቃዱን ያገኙ አካላት ያሏቸውን መብቶችና ግዴታዎችንም አስቀምጧል፡፡

በመመሪያው መሰረት ከተቀመጡት መብቶች መካከል ማንኛውንም የምርጫ ሂደት ማለትም የመራጮች ምዝገባ፣
የእጩ ምዝገባ፣ የምርጫ ቅስቀሳ፣ የድምጽ አሰጣጥ፣ የቆጠራ ሂደት እና የውጤት አገላለጽን መከታተልና መዘገብ ይገኝበታል፡፡

ጠቅላላ የድምጽ አሰጣጥ ሂደትን እና የመራጮች ምዝገባን የተመለከቱ መረጃዎች በሚስጥር ስለመያዛቸዉ እንዲሁም የድምጽ አሰጣጡን ሚስጥራዊነት መዘገብ እንደሚችሉ ነው የተነገረው፡፡

የምርጫ ሂደቱን በማያውክ መልኩ በምርጫ ጣቢያዎች የመዘዋወር ፣ ከቦርዱና ከአካባቢ ባለስልጣናት እንዲሁም ከምርጫ አስፈጻሚ አካላት መረጃና ትብብር ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡

ከእነዚህ መብቶች ባለፈ መገናኛ ብዙሃኑን የተመለከተው መመሪያ ሃላፊነቶችን አስቀምጧል፡፡

በዚህም መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ በመሆን ከመጥላት ወይንም ከመደገፍ የተቆጠቡ ዘገባዎችን መስራት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡

ምርጫዉን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች የማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አባል አለመሆናቸው መረጋገጥ እንዳለበትም ነው የተገለፀው፡፡

የምርጫ ሂደትን ከምርጫ ጣቢያው በ200 ሜትር ርቀት ዙሪያ ውስጥ ለመዘገብ ፈቃድ መጠየቅና እውቅና ማግኘት እንደሚያስፈልግም ተጠቁሟል፡፡

እንዲሁም የማንኛውንም ፓርቲ አርማና መቀስቀሻ ምልክት አድርገዉ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው የተገለፀ ሲሆን መገናኛ ብዙሃኑ እውነታን አፈላልገው ይንም አጣርተው መዘገብ ይኖርባቸዋል ተብሏል፡፡

ከምርጫው በፊት የምርጫ ቅድመ ትንበያ መረጃ ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ቅድመ ግምት የተቀመጠ ሲሆን ሆኖም በምርጫው እለትና ጊዜያዊ ውጤት ይፋ እስከሚሆንበት ጊዜ ድረስ የተከለከለ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

መመሪያው በልዩ ድንጋጌው መገናኛ ብዙሃኑ በምርጫ ዘመቻ ወቅት መቻቻልና ነጻ ክርክር እንዲረጋገጥ ተገቢውን ሁሉ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸዉ አስቀምጧል፡፡

ውይይቱን አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ የነበራቸው የቦርዱ የቦርዱ የኮሙዩኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ውይይቱ ሰፊ ግብአት የተገኘበት እና በቀጣይ ውይይቶች ዳብሮ ከሌሎች መመሪያዎች ጋር ጸድቆ ወደ ስራ ይገባል ብለዋል።

በሃብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.